ቀጥታ፡

የኤርትራ የባህል ቡድን ባህር ዳር ከተማ ገባ

ባህር ዳር  የካቲት 8/2011 በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ዳግም የተፈጠረውን የሰላም ግንኙነት ለማጠናከር ትላንት አዲስ አበባ የገባው የኤርትራ የባህል ቡድን ባህር ዳር ከተማ ገባ።

ዛሬ እኩለ ቀን ላይ 63 አባላትን ያካተተው የባህል ቡድን ባህር ዳር አየር ማረፊያ ሲደርስ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አርቲስቶች አቀባበል አድርገውለታል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኤርትራ የባህል ቡድን ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ከተማ ቆይታ ያደርጋል።

"በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተፈጥሮ በነበረ ቁርሾ በሁለቱ  ሀገራት የሚኖሩ አንድ ህዝቦች ከ20 ዓመታት በላይ በአንድ ላይ ማክበር የተውትን የባህልና የሙዚቃ ትርኢት ዳግም ለማስጀመር ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል" ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ በሚቀርበው ትርኢት የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ማንነት ማሳያ የሆኑ የባህልና የሙዚቃ ትርኢቶችን ለማሳየት ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

ትርኢቱ  በታሪክ አጋጣሚ ተነጣጥለው የነበሩ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦችን እንደ አዲስ ለማቀራረብ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የባህል ቡድኑ አባላት የህዝብ ለህዝብ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ትርኢቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ የባህር ዳር ከተማን ታሪካዊ ቦታዎችና የኢንዱስትሪ መንደሮች እንደሚጎበኙም ተገልጿል።

የአማራ ክልል የምንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስበበኩላቸው " የኤርትራ የባህል ቡድን ልኡካን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት እንደገና መጀመሩን ዳግም ያበሰረ ነው" ብለዋል።

ጉብኝቱ ተለያይተው የነበሩ የሁለት አገር አንድ ህዝቦች ዳግም ወደ ነበረ ፍቅራቸውና ሰላማቸው መመለሳቸውን በኪነ-ጥብቡ አጉልቶ ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኤርትራ ባህል ቡድን ልኡክ መሪ አቶ ሚካኤል ተፈሪ በበኩላቸው የባህል ቡድኑ የተደረገለት ቤተኛ አቀባበል እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ የባህል ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሰላማዊ ግንኙነቱን በኪነ-ጥበብ ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።

"በባህልና በእምነት አንድ የነበሩ ህዝቦች ለዘመናት ተለያይተው መኖራቸው የኤርትራን ህዝብ ሰላም ነስቶት ኑሯል" ያሉት ቡድን መሪው፣ ግንኙነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ኪነ-ጥበባዊ መልክት እንደሚተላለፍ ተናግረዋል።

የባህል ቡድኑ መሪ አቶ ሚካኤል ተፈሪ እንዳሉት የባህል ቡድኑ በነገው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ኪነ-ጥበባዊ ኮንሰርቱን ያቀርባል።

በመጪው የካቲት 10 ቀን 2011 በአዳማ ከተማ እንዲሁም የካቲት 12 ቀን 2011 በሃዋሳ ከተማ የሚያቀርብ ሲሆን የመዝጊያ ኮንሰርቱን በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።

የባህል ቡድኑ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ባህር ዳር አየር ማረፊያ ሲደርስ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አርቲስቶች አቀባበል አድርገውለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም