በአዲስ አበባ ስጦታ እቃ ሻጮችና ጋላሪዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ ቅርሶችን ለገበያ ይቀርባሉ ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ስጦታ እቃ ሻጮችና ጋላሪዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ ቅርሶችን ለገበያ ይቀርባሉ ተባለ

አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 በአዲስ አበባ የስጦታ ዕቃዎች ለገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ የአገር ቅርሶችም ለሽያጭ የሚቀርቡበት አጋጣሚ መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በከተማው የሚገኙ የስጦታ እቃ ነጋዴዎችና ጋላሪዎች የስጦታ እቃን ከቅርስ ለይቶ ለገበያ የማቅረብ ስራዎቻቸውን ለማጤንና ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል።
ጥናቱ የተካሄደው በአምስት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 100 የስጦታ እቃ ሻጮችና ጋላሪዎች ላይ ነው።
በጥናቱ መሰረት በስጦታ እቃ ሽያጭና ጋላሪ ስራ ከተሰማሩት 43 በመቶ የሚሆኑት ለገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች የአገር ቅርስ ስለመሆናቸው እውቀት የላቸውም።
በባለስልጣኑ የቅርስ ቁጥጥርና ደንብ ማስከበር ባለሙያ አቶ ዋናው ኃይለ ማርያም እንደገለጹት ነጋዴዎቹ "ቅርሶች የሚገኙት በሃይማኖት ተቋማትና ሙዚየሞች ብቻ ነው" የሚል አስተሳሰብ ያላቸው በመሆኑ እቃዎቹን ለገበያ የሚያቀርቡት የተሰሩበትን ቁስና ክብደት በማየት ብቻ ነው።
በመሆኑም ቅርሶች ከስጦታ እቃ ጋር ተቀላቅለው የሚገኙበትና ለሽያጭም የሚቀርቡበት አጋጣሚ እንዳለ ተናግረዋል።
ጥናቱ እንደሚየሳየው 44 በመቶ የሚሆኑት ነጋዴዎች አሮጌ የሆኑ ዕቃዎችን ባለመግዛትና ባለመሸጥ ቅርሶች ለገበያ ሊቀረቡ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር ይከላከላሉ።
እንደ አቶ ዋናው ገለጻ 13 በመቶ የሚሆኑት ቅርስ የሚመስሉ ምርቶች በሚያጋጥማቸው ወቅት በሚመለከተው አካል በኩል እንዲጣራ ያደርጋሉ።
በሌላ በኩል 90 በመቶ የሚሆኑት ተቋማት የዕደ ጥበብ ምርቶችን በሚገዙበት ወቅት ደረሰኝ እንደማይቀበሉ ጥናቱ አረጋግጧል።
ይህም ምንጩ የማይታወቅ እቃ ቅርስ ላለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆን የሚያስቸግር ከመሆኑም በላይ ቅርሶች በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ እንዳይቀርቡ በሚደረገው ጥረት ላይም እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።
ቱሪስቶች ለገዙት እቃ ደረሰኝ ስለማይሰጣቸው እቃው በጥርጣሬ ሲያዝ በቱሪስቶች ላይ እንግልት እየፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዘርፉ የተሰማሩት ተቋማት ምርቶችን ሙሉ አድራሻቸው ከሚታወቁ ተቋማት እና ተጠያቂነት ካላቸው አምራቾች መግዛት፤ ቱሪስቶችም ለገዙት እቃ ዋስትና ወይም ደረሰኝ መስጠት እንደሚገባቸውም በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።
ከተቋማቱ ውስጥ 66 በመቶ የሚሆኑት ስለ ቅርስ ምንነት የግንዛቤ መጨበጫ ወስደው እንደማያውቁም ጥናቱ አሳይቷል።
በመሆኑም ተቋማት ላይ የግንዛቤ የመፍጠርና የጋራ መግባባት ስራ ማከናወን ህገወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል ያገዛልም ተብሏል።
በመገናኛ ብዙሃን ስለ ቅርስ ምንነትና ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውር ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል በወጡ ህጎች መሰረት ቁጥጥርና ህጋዊ እርምጃ መውሰድና የስጦታ እቃዎች አምራቾችንና ሻጮችን መደገፍ እንደሚገባም ተገልጿል።
በዘርፉ የተሰማሩት ተቋማትም ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውር ላይ በመንግስት የሚሰሩ ስራዎችን ማገዝ ፣አጠራጣሪ ነገር ሲኖር ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠትና ለሽያጭ የሚቀርቡ እቃዎች የቅርስነት እሴት የሌላቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸውም በጥናቱ ተመልክቷል።
በቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ 209/1992 መሰረት ቅርሶችን ሆነ ብሎ የሰረቀ፣ ያፈረሰና ለህገ-ወጥ ተግባር እንዲዉሉ ያደረገ ከ13-20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተደንግጓል።