ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን አቤቱታ ውድቅ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን አቤቱታ ውድቅ አደረገ
አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ አደረገ።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በ47 የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ክስ መስርቷል።
ተከሳሾቹ ከሐምሌ 26-30 ቀን 2010 ዓ.ም ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በፈጠሩት ግጭት 59 ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግለሰቦች ቤቶችና የተለያዩ የንግድ ተቋማት ተቃጥለው እንዲወድሙ በማድረግ ከ412 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተጠቁሟል።
በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረጋቸውም ከቀረበባቸው ክስ መካከል ተጠቃሽ ነው።
አቃቤ ሕግ በእነዚህና ሌሎች ወንጀሎች ላይ 213 ምስክሮች እንዳሉት ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
በእነዚህና ሌሎች ወንጀሎች ክስ የቀረበባቸው አቶ አብዲ መሐመድም አቃቤ ሕግ አለኝ ያላቸው ምስክሮች ስምና አድራሻ እንዲሰጣቸው በጠበቃቸው በኩል ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
አቃቤ ሕግ በበኩሉ "ምስክሮቼ ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት ስምና አድራሻቸውን ግልጽ ማድረግ የሕግ ድጋፍ የሌለውና ለአደጋ የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ለተከሳሽ ጠበቃ ስም ዝርዝራቸውን መስጠት አልችልም" ሲል ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የአቶ አብዲ መሃመድ ጠበቆች የምስክሮች ስምና አድራሻ እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ውድ አድርጎታል።
ፍርድ ቤቱ አቶ አብዲን ጨምሮ በእርሳቸው መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾችም ለየካቲት 20 ቀን 2011 ዓ.ም መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል።