ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጥር ወር 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግብይት ፈፅሟል

አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  ባለፈው ጥር ወር ብቻ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ።

ከግብይቱ ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ የያዙት የሰሊጥና የቡና ምርቶች ናቸው።

በተጠቀሰው ወር 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሰሊጥና 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የቡና ግብይት መከናወኑን የምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።  

በአጠቃላይ በወሩ ለግብይት የቀረበው የግብርና ምርቶች መጠን ከ74 ሺህ ቶን የሚልቅ ሲሆን ሰሊጥ 43 በመቶ የግብይት መጠን እና 41 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ትልቁን ድረሻ ይዟል።

በተጠቀሰው ወር ለገበያ የቀረበው ሰሊጥ ከ32 ሺህ ቶን በላይ ሲሆን አብዛኛውም የሁመራ ነው። አማካይ የሰሊጥ ዋጋም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በወሩ ከ27 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለገበያ ቀርቦ 1 ነጥበ 8 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን ከ10 ሺህ የሚበልጥ ነጭ ቦለቄም ለግብይት ቀርቧል። 

ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው አኩሪ አተር በጥር ወር 4 ሺህ 632 ቶን ለግብይት ቀርቦ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግብይት ተፈፅሞበታል።

በአኩሪ አተርና እና በቡና ምርት የታየው ሽያጭ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የምርት ግብይት መጠኑ ቅናሽ አሳይቷል።

ነጭ ቦሎቄ ከታህሳስ ወር ግብይት ጋር ሲነጻጸር በግብይት መጠንና ዋጋ በአስር በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፤ በአማካይ ዋጋውም 2 በመቶ ቅናሽ አስመዝግቧል።

በተመሳሳይ የቡና ግብይት መጠንና ዋጋ አፈጻጸም ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ሁለት በመቶ ቀንሷል፤ እንዲሁም ቦለቄ የግብይት መጠን ስምንት በመቶ፣ የግብይት ዋጋው ደግሞ አስር በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም