ቀጥታ፡

በጅግጅጋ ነገ ለሚጀመረው 8ኛው የከተሞች ፎረም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል

በጅግጅጋ የካቲት 8/2011 በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ለሚካሄደው 8ኛው የከተሞች ፎረም አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ “መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ነገ የካቲት 9 ቀን 2011 ለሚጀመረው የዘንድሮው የከተሞች ፎረም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። 

በዚህ ጊዜ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ እንደገለፁት በዘንደሮው የከተሞች ፎረም ላይ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናትን ጨምሮ የተለያዩ  ሁነቶች ይከናወናሉ።

በፎረሙ ላይ 168 የአገር ውስጥ ከተሞችን ጨምሮ የጅቡቲ ዋና ከተማ፣ የሶማሌላንድ በርበራና ሀርጌሳ ከተሞችም ይሳተፋሉ በለዋል።

የሁሉም ከተሞች የልኡካን ቡድን አባላት ወደ ጅግጅጋ መግባታቸውንም ገልፀዋል።

ከፎረሙ ጋር በተያያዘ በጅግጅጋ ስታድየም ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚ የሚገኝበት የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

ስለጅግጅጋ ከተማ ሁሉን አቀፍ ግንዛቤ እንዲኖር የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ጥናታዊ ፅሁፍ ከ1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሚገኙበት ይቀርባል።

በተለይም በፎረሙ ላይ በከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የመሬት ልማትና ማናጅመንት፣ በአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ቤቶች ግንባታ ላይ ያተኮሩ 24 ጥናታዊ ፅሑፎችም ይቀርባሉ። 

ከተሞችን በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝም እና በመሳሰሉት ለማስተዋወቅ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡና ሞዴል የሚሆኑ ከተሞች የሚሸለሙበት መርሃ ግብርም መዘጋጀቱ|ን አቶ ካሳሁን ገልፀዋል።

የጅግጅጋ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ ሼህ ቢ በበኩላቸው እንደተናገሩት ፎረሙ በጎ ገፅታ ለመገንባትና አንድነትን ለማጠናቀር ከፍተኛ ሚና አለው።

የፀጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ ለማድረግ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይል፣ ከመከላከያና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አስፈላጊው ስራ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።

ከአራት አመታት በፊት 972 የነበሩት የአገሪቱ ከተሞች በአሁኑ ወቅት 2032 መድረሳቸውን ከሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም