ቀጥታ፡

ተቀራርበን በመስራት የመከላከያ ሰራዊታችንን ጫና እናቃልላለን---ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዳማ የካቲት8/6/2011 ከመወቃቀስ ይልቅ ችግሮቻችንን በውይይት በመፍታትና ተቀራርበን በመስራት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የሚፈጠረውን አላስፈላጊ ጫና ለማስቀረት እንሰራለን ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ ።

ፓርቲዎቹ የመከላከያ ሰራዊታችንን ልናከብረው ፣ልናፈቅረውና ልንደግፈው ይገባል ሲሉ  በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሔ በሰጡት አስተያየት የመከላከያ ሰራዊት እንደ ተቋም ገለልተኛ መሆን አለበት ።

ተቋሙ ማንም የሚያፈርሰውና ሌላ ሲመጣ የሚገነባው ሳይሆን ጠንካራ ቁመና የተላበሰ አገራዊ ተቋም ሆኖ መቀጠል አለበት የሚል አስተሳሰብ እንዳላቸው ተናግረዋል ።

“ህብረተሰቡም ሆነ እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ችግር ሲመጣ እጃችንን የምንቀስረው በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ነው” ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር “ነገር ግን እየሞተም እየቆሰለም ያለው ለእኛ ሲል መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል” ብለዋል ።

ሰራዊቱ ከማህበረሰቡ የወጣ እንደመሆኑ ሀገርና ህዝቡን የመጠበቅ እንጂ ወገኖቹ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም እንደማይሻ ገልጸው “አንዳንድ ፖለቲከኞች በዚህ መንገድ ለማግኘት የምንፈልገው የፖለቲካ ትርፍ መቅረት አለበት” ሲሉ ገልፀዋል ።  

የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በማበላሸትና ሃገራዊ እንቅስቃሴውን በማጉደፍ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም እንደሌለ በማወቅ ለተልዕኮው መሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አቶ ገብሩ ተናግረዋል።

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትእግስቱ አወሉ በበኩላቸው ሃገሪቱ በምሰራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ስም ያለው የመከላከያ ሰራዊት ያላት መሆኑን ገልፀዋል ።

ከዓመት በፊት በነበረው የሃገር ውስጥ አለመረጋጋት ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ እንደሌሎች ሃገሮች ስልጣንን በሃይል ለመያዝ ከመሞከር ይልቅ በታላቅ ኃላፊነት ሃገሪቱን የማረጋጋት ስራ ማከናወኑ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

“አሁን ለሚታየው አንፃራዊ ሰላም ያበቃን ህዝባዊ ወገንተኝነት ተላበሶ ችግሮችን በመጋፈጥና ለአገርና ለሰላም በመቆም እየሞተና እየቆሰለም ጭምር ነው”ብለዋል።

ለህዝባዊነቱ ምስጋና ሲገባው ስሙን ለማጉደፍ ይደረግ የነበረው ጥረት የተሳሳተ መሆኑን ገልጸው “የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጭ ብለን በመወያየትና ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለመከላከያ ሰራዊታች አላስፈላጊ ጫና ከመፍጠር ልንታቀብ ይገባል”ብለዋል

የኢትዮጵያ ራእይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብሮ እንዳሉት በፊት የነበረው ስርዓት ችግር ስለነበረው የመከላከያ ሰራዊቱን የሚያውቁት በሩቁ ብቻ ነበር ።

አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጊቢን ጨምሮ ጓዳውን ማየታቸውንና እያካሄደ ባለው ተቋማዊ ሪፎርም ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

https://www.youtube.com/watch?v=LD4XgkbcL4g&t=394s

“ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ  የቆመ መከላከያ ሰራዊት አድርጎ የማየት የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደነበር” የገለፁት የራእይ ፓርቲ ሊቀመንበር ከፊት ለፊት የነበሩት ፖለቲካዊ አመራሮችን በማየት ብቻ ሰራዊቱ መፈረጅ ተገቢ እንዳልነበረ ገልፀዋል ።

አሁን ግን ሰራዊቱ በጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም ዴሞክራሲያዊነቱ ፣ ግልፅነቱና አሳታፊነቱን በቅርበት ስለተገነዘቡት ልዩ ክብር እንደሚሰጡት ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብም የመከላከያ ሰራዊቱን እንዲወድ ፣ እንዲያከብር፣ እንዲንከባከብና አካሉ አድርጎ እንዲመለከት አቶ ተሻለ ሰብሮ አሳስበዋል ።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት የመከላከያ ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ የሚሞት መሆኑ ቢታወቅም ከስርዓቱ ጋር ያለው ትስስር በሚከፍለው መስዋእትነት ልክ እንዳይመሰገን አድርጎት ቆይቷል ።

“ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን” ያሉት ሊቀመንበሩ ”ስርዓት በተቀየረ ቁጥር የሚካብና የሚናድ መሆን የለበትም ” ብለዋል ።

”መከላከያ ሀገር እንጂ ብሔር የለውም” በሚለው አስተሳሰብ ዙሪያ ጠንካራና ተከታታይነት ያለው ስራ መሰራት እንዳለበትም አቶ የሺዋስ አሰፋ ተናግረዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ትናንት በአዳማ ከተማ ”ህገ-መንግስታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረው ተቋማዊ ለውጥ እናስቀጥላለን ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው 7ኛው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ላይ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልእክት “በሰራዊቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ ፍረጃ መቅረት አለበት ማለታቸው” ይታወሳል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም