ቀጥታ፡

የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሣምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ጥር 8/2011 የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።

ነገ ረፋድ ላይ ከምባታ ዱራሜ የአምናውን የሊጉን አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ዱራሜ ላይ ያስተናግዳል።

ከነገ በስቲያም ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከድሬዳዋ ከተማ፣ 4 ሠዓት ከ30 ላይ መከላከያ ከቡታጅራ ከተማ ይጫወታሉ።

ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት ይጋጠማሉ።

በስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር መቐለ ሰብዓ እንደርታና ፌዴራል ፖሊስ ጨዋታ የማያደርጉ በመሆናቸው አራፊ ናቸው።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10 የእጅ ኳስ ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረውና ስድስት ቡድኖች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ የወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት አዳማ ከተማን 58 ለ 35 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ሁሉንም ክለቦች በአንድ ምድብ በማካተት በዙር ያካሂድ የነበረውን የውድድር ፎርማት በ2011 ዓ.ም በመቀየር ቡድኖች በሁለቱም ጾታዎች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ፎርማት አዘጋጅቷል።

በውድድሩ ፎርማት መሰረት በወንዶች ፕሪሚየር ሊግ በምድብ አንድ የተደለደሉት ሶስቱ ክለቦች ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው ጨዋታ ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትና አዳማ ከተማ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ነገ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ከነገ በስቲያ አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት ይጫወታሉ።

በወንዶችና በሴቶች የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በተመሳሳይ በምድብ ሁለት የሚገኙት ቡድኖች በጎንደር ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ይህን አዲስ የውድድር ፎርማት መከተል ያስፈለገው ክለቦች ብዙ ውድድሮችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲያካሂዱ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በተጨማሪም ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ መከላከያ አዲስ አበባ ፖሊስን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከነገ በስቲያ በስድስተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ተስተካካይ መርሃ ግብር ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከሙገር ሲሚንቶ ከጠዋቱ 3፡00 ሠዓት ላይ ይጫወታሉ።

በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም