የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቆይታ ወጣቶች ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ትስስር እንዲገነዘቡ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቆይታ ወጣቶች ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ትስስር እንዲገነዘቡ ያስችላል
አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ቆይታ ወጣቶች የአገራቱ ትስስር ምን ይመስል እንደነበር እንዲገዘቡና ጠንካራ ግንኙነት እንዲመሰርቱ እንደሚያግዝ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።
የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የባህል ልዑክ በኢትዮጵያ የአንድ ሳምንት ቆይታ ለማድረግ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።
በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለኢዜአ እንደተናገሩት ኪነ-ጥበብ ለህዝብ ስሜት ቅርብ በመሆኑ በዚህ በኩል የሚከናወኑ ተግባራት በተለይ የሁለቱን አገራት ወጣቶች ትስስር ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ አለው።
ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት እንደገና በመጀመሩ ትልቅ ደስታ መፍጠሩንና በቀጣይም የኢትዮጵያ የባህል ቡድን ተመሳሳይ ጉብኝትና ስራዎችን በኤርትራ እንዲያቀርብ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመዋል።
በልዑኩ ውስጥ በርካታ ልምድ ያላቸው ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች መካተታቸውንም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።
የልዑኩ አባል የሆነው እዮብ ሀብተአብ የሙዚቃ ባለሙያ ነው፤ 'ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት የሠላም ጉዞ የተቃና እንዲሆን በስራችን ለማገዝ ኢትዮጵያ ተገኝተናል' ብሏል።
የኤርትራዊያንን ባህል ለኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህቶች ለማሳየት መዘጋጀታቸውን ገልጾ ይህም የአገራቱን ባህል የማሳደግ ሚና እንደሚኖረው አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወጣት ሚናስ በላይ በበኩሉ የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ስራዎች በካሴትና በሲዲ እንጂ በአካል እንዳማያውቃቸው ገልጿል።
''አሁን ሁሉም ነገር ሠላም ሆኖ በአካል ለማየትና ከኢትዮጵያዊያን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ለመስራት መምጣቴ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል'' ነው ያለው።
ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል ለማድረግ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኘው አርቲስት ንዋይ ደበበም 'አገራቱ ብዙ ነገሮችን አሳልፈዋል፤ አሁን ጊዜው የፍቅር ነው' ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከኤርትራዊያን አርቲስቶች ጋር ለጋራ ዓላማ መስራት ደስታን እንደሚሰጥ የገለጸው ንዋይ 'በዚህ ሂደት አገሬን እንደ አምባሳደር ሆኜ በማገልገሌ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል' ሲል ተደምጧል።
የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የባህል ልዑክ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ሲደርስ የውጭ ጉዳይ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አቀባበል አድርገውለታል።
በሚካኤል ተፈሪ የተመራው የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የሙዚቃ ስራዎች በተለይም ሁለቱ አገራት በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ስራዎችን ያቀርባል።
ለመርሃ ግብሩ አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ አዳማና ሀዋሳ የተመረጡ ሲሆን ከኢትዮጵያ የባህል ቡድን ጋር ስራዎች እንደሚያቀርቡ ተነግሯል።
የኤርትራ የባህል ቡድን የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም 25 ሺህ ህዝብ የሚያሳትፍ የማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሚለኒየም አዳራሽ እንደሚያቀርብም ይጠበቃል።