በቀጣናው የጦር ሰፈር ባቋቋሙ አገሮች የሚደረገው ፉክክር በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣናው የጦር ሰፈር ባቋቋሙ አገሮች የሚደረገው ፉክክር በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል
አዲስ አበባ የካቲት 7/2011 በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ወታደራዊ የጦር ሰፈር ባቋቋሙ አገራት መካከል የበላይነት ለመቀዳጀት የሚደረግ ፉክክር ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በምታደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ምሁራን ገለጹ።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ቱርክ፣ አሜሪካና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በጅቡቲ የየራሳቸውን ወታደራዊ የጦር ሰፈር መስርተዋል።
በአካባቢው በተመሰረቱት የጦር ሰፈሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት ያሰማራችው አሜሪካ ስትሆን ፈረንሳይ በሁለተኝነት ትከተላለች።
የዓለም አቀፍ የባህር ንግድ ትራንስፖርት ዋነኛ መተላለፊያ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ በተለይም በስዊዝ ካናል በኩል ከዓረብ ሰላጤ አገራት ለሚጓጓዘው የነዳጅ ምርት ዋነኛ መንገድ ነው።
በየቀኑ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በዚህ የባህር መስመር ይጓጓዛል።
አገራቱ የጦር ሰፈር ለመመስረት የሚያቀርቡት ጥያቄ አንዱ ምክንያትም በአካባቢው የሚካሄደውን የባህር ላይ ውንብድና እና ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚያስችል ድጋፍ ለመስጠት ነው።
የፖለቲካ ምሁራንና ተንታኞች ግን በአፍሪካ ቀንድ ካለው መልክዓ ምድራዊ የፖለቲካ ጥቅም አኳያ አገራቱ በአካባቢው የበላይነትን ለመቀዳጀት ፉክክር በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ፍቃደ ተረፈ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቀጣናው የተቋቋሙ የጦር ሰፈሮች ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በምትጫወተው ጉልህ ሚና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ አኳያ በቀጣናው ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ዙሪያ ያሉ እንቅስቃሴዎች ጥንቃቄና ምላሽ በሚሰጥ መልኩ መቃኘት እንዳለበትም ገልጸዋል።
በጥንታዊት ቻይና ስልጣኔ የነበረውን ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር መልሶ ለመዘርጋት በቅርቡ የአገሪቱ መንግስት ''የሐር መንገድ'' የተባለውን የንግድ ፖሊሲ ይፋ አድርጓል።
ፖሊሲው ቻይና በ68 የአውሮጳ፣ የእስያና የአፍሪካ አገራት የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚያስችላት እንደሆነም ይነገራል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ታፈሰ ኦሊቃ በበኩላቸው በአሜሪካና በቻይና መካከል የምጣኔ ሀብት የበላይነት ለማስጠበቅ የነበረውን ፍጥጫ ለአብነት አንስተዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ያቋቋሙ አገሮች በአካባቢው ያሉትን አካባቢያዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የቀጣናውን አገራት ተጎጂ እንደሚያደርጋቸው ዶክተር ታፈሰ አስረድተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ የፀጥታና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ እንደሚሉት ደግሞ የቀጣናው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሽብርተኝነትና ህገ-ወጥ የባህር ላይ ውንብድናን ለመቆጣጠር አመቺ በመሆኑ አገራቱ ወታደራዊ የጦር ሰፈር እንዲያቋቁሙ ያስገደዳቸው አበይት ምክንያት ነው።
በቀጣናው ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋም የሚደረገው ሩጫ በአካባቢው ያለው ሰላምና ደህንነት ጉዳይ እንደሆነ ያብራሩት ኮማንደር አበበ በተለይ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከቱርክ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የከተታቸው ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል።
የቀይ ባህር አካባቢ ጉዳይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ፈተና መሆኑ የሚቀጥል ነው የሚሉት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የቀድሞው የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ ናቸው።
የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ዲፕሎማቱ አምባሳደር ተቀዳ 'የውይይት፣ ምርምርና ትብብር ማእከል' በሚታተመው ጆርናል ባሰፈሩት ትንታኔ "በአካባቢው ያለው ሁኔታ በእጅጉ እየተለወጠ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለም፤ የቀይ ባህር ደግሞ በአካባቢው ጉዳዮች ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን የዓለም ክፍሎች እንደ ማግኔት እየሳበ የመልክዓ-ምድራዊ ፖለቲካውን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየከተተው ነው" ብለዋል።