የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ  የካቲት 7/2011 የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩ.ኤስ.አይ.ዲ/ በአራት ሚሊዮን ዶላር የተገዙ የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶች ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ በቅዱስ ጳውሎስና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችና በታዳጊ ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ለሚገኙ እናቶችና ህጻናት የህክምና አገልግሎት እንደሚውል ተገልጿል።

ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ድጋፉ ተደራሽ የሚሆኑባቸው ክልሎች ናቸው።

የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶቹ ርክክብ የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን፣ የዩ.ኤስ.አይ.ዲ የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ አሊሲያ ዲነርስታይን እንና የሆስፒታሎቹና የክልሎቹ ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከናውኗል።

ከህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶቹ በተጨማሪ ለጤና ባለሙያዎች ስለ መድሃኒቶቹ አጠቃቀምና ስለ ህክምና ቁሳቁሶቹ ጥገና ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

መድሃኒቶቹ የሚውሉት የመተንፈሻ አካላት ችግር ለሚያጋጥማቸው ህጻናት እና የደም ግፊትና የሳምባ በሽታ ላለባቸው እናቶችና ህጻናቶች እንደሆነ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ አሊሲያ ዲነርስታይን ገልጸዋል።

ድጋፉ በሆስፒታሎቹና በክልሎቹ ያለውን የጤና ችግር እንደሚያቃልልና የተሻለ የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ከመንግስት የጤና ፖሊስ ጋር የሚጣጣምና በእናቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የጤና አገልግሎቶችን ፍትሃዊ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶቹ ጥራት ያላቸው በመሆናቸው ሚኒስቴሩ ጥራት ያለው አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት የያዘውን ራዕይ ለማሳካትም ያግዛል ነው ያሉት።

የተደረገው ድጋፍ በቀጥታ ለተጠቃሚው ህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ሆስፒታሎችና የክልሎች ጤና ቢሮዎች አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ለወባ፣ ሳምባ፣ የደም ግፊትና ሌሎች በሽታዎችን መከላከል፣ ለእናቶችና ህጻናት ጤና እንዲሁም ለውሃና የንጽህና አገልግሎት የአራት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም