ቀጥታ፡

''የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር አለኝታነቱን እያስመሰከረ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ክብር ይገባዋል''-ጠ/ሚ ዓቢይ

አዳማ የካቲት 7/2011 ለአገርና ለሕዝቡ ቅድሚያ በመስጠት ውድ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር አለኝታነቱን እያስመሰከረ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ተገቢው ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ያሉት ''ሕገ መንግሥታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረው ተቋማዊ ለውጥ እናስቀጥላለን!'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲዬም በተከበረው ሰባተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ እንደገለጹት ሠራዊቱ ለጠላቶች የፍርሃት ምንጭ ለወዳጆችና ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ሁሌም ኩራት ነው ብለውታል።

በውጭም ሆነ በውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች በከፍተኛ ወኔና ቁርጠኝነት በብቃት በመወጣት ተልዕኮውን እየፈፀመ ላለው ሠራዊት ክብር በመስጠት ሞራሉን ሊጠብቅለት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሠራዊቱ በሰላም ማስከበር ተግባር በተሰማራባቸው አገሮችና ሕዝቦች ሁሉ በቁርጠኝነትና በሕዝባዊ ወገንተኝነት አኩሪ ተግባር መፈፀሙን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ እንደ ተቋም ክፍተቶቹን በየጊዜው እየሞላ የአገር አለኝታነቱን በማጠናከር በዘላቂነት የሚቀጥል እንጂ፤ በዜሮ ሂሳብ እየተባዛ ወደ ኋላ የሚመለስበት ምክንያት ሊኖር አይገባም ብለዋል።

''አፈርሶ መገንባት ወደኃላ እንጂ ወደፊት አያራምድም'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ፣ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በየጊዜው ሊቀያየር ከሚችለው ሥራ አስፈፃሚ አካል ጋር ሳይወጣና ሳይወርድ የሚቀጥል ሠራዊቱ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን እየተገነባ ያለው የመከላከያ ሠራዊት የአገር ሉአላዊነት ስለሚጠብቅ ክብር እንዲሰጡት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎችም የሠራዊቱን ሞራል በሚያነቃቃና ክብሩን በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በመሰማራት እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በበኩላቸው ዘመናዊና ፕሮፌሽናል ሠራዊት ለመገንባት የተጀመረው ሪፎርም ተልእኮውን በብቃት የሚያስፈጸምበት የተሟላ ቁመና እንደሚያላብሰው አብራርተዋል።

በዓሉ ለአገርና ለሕዝብ ሲሉ የተሰው የሠራዊቱ አባላት ለመዘከር፣ ለቀጣይ ተልዕኮው ሠራዊቱ ቃሉን እንዲያድስና አለኝታነቱን የሚያጠናክር  መነሳሳት ለመፍጠር ነው ተብሏል።

የዘንድሮውን መከላከያ ሠራዊት ቀን በድምቀት እንዲከበር የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድርና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ምስጋና አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳ ''እንግዶቻችን በክብር ተቀብለን በፍቅር ለማስተናገድና በዓሉን በጋራ ለማክበር በመብቃታችን ልባዊ ደስታ ተሰምቶኛል'' ብለዋል።

የሠራዊቱን ስም ለማጠልሸት የሚደረገውን ማንኛውንም የፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ በማክሸፍ ሕዝቡ ተገቢው ፍቅርና ክብር በመስጠት ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ አፈጉባኤዎች፣ሚኒስትሮች፣አባገዳዎች ፣የሃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች ፣ታዋቂ ግለሰቦች፣ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የአዳማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የአየር ኃይል ሚጎችና ሄሊኮፕተሮች የኮማንዶ አባላትና የአዳማ ከተማ የማስ ስፖርት ህፃናት ያቀረቧቸው ትርኢቶች ለበዓሉ ድምቀት ልዩ ድባብ ፈጥረው ውለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም