በደሴ ከተማ በ29 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ሥራ ጀመረ

77

ደሴ ጥር 7/2011 በደሴ ከተማ በ29 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን 125 ተማሪዎች እያስተማረ መሆኑን አስታወቀ።

የትምህርት ቤቱ  ወጪ የፍሊንት ስቶን ሆምስ ኢንጅነሪንግ ባለቤት ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ ሸፍነዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ በለጠ ኃይሌ  እንደገለጹት ''ይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ትምህርት ቤት'' ተብሎ የተሰየመው ተቋም ተማሪዎቹን ከየካቲት 4/2011 ጀምሮ እያስተማረ ነው።

ትምህርት ቤቱ በአማራ ክልል ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎችን ለመለየት የሚያስተምር ሲሆን፣ተወዳዳሪ ምሁራንን ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና  ከ85 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በመመልመል በማስተማር ላይ ይገኛል። ከነዚህም 26ቱ ሴት ተማሪዎች ናቸው።

ትምህርት ቤቱ እስከ 400 የሚደርሱ የሁለተኛና ደረጃ ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የተናገሩት ርዕሰ መምህሩ፣ በአንድ የመማሪያ ክፍል ከ28 እስከ 31 ተማሪዎች እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮና ከአማራ ልማት ማህበር( አልማ) በተገኘ 11 ሚሊዮን ብር ወጪ የመማሪያ ቁሳቁስ እንዲሟላለት መደረጉን አስታውሰዋል።

ትምህርት ቤቱ ዘመናዊ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ-መጻህፍት ፣የመመገቢያ አዳራሽና የተማሪዎችን ማደሪያ ቤት ጨምሮ 13 ሕንጻዎች እንዳሉትም ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ መምህርት ፋጡማ ዓሊ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ሙሉ ቁሳቁስ ተሟልቶለት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የአልማ ደሴ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አበባው ታደሰ በበኩላቸው ባለሀብቱ በ2002 በገቡት ቃል መሠረት ትምህርት ቤቱን መገንባታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም