ቀጥታ፡

የትምሀርትና ስልጠና ሥርዓቱ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባለማድረጉ የሚፈለገውን ውጤት አልተገኘበትም-ፌዴሬሽኑ

አዳማ የካቲት 7/2011 በሥራ ላይ ያለው የትምሀርትና ስልጠና ስርዓት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባለማድረጉ የሚፈለገውን ውጤት እንዳልተገኘበት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለፀ።

የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ቅሬታው ትክክል በመሆኑ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳመለከቱት በሥራ ላይ ያለው ሥርዓተ ትምህርት የአካል ጉዳቶች ተደራሽነትን ታሳቢ አላደረገም።

''ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ያልሆነ የትምህርት መሠረተ ልማት መንስዔው ከአመለካከት ችግር ይመነጫል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ማየት የተሳናቸው ያለ ምልክት ቋንቋ ፣ ዓይነስውራን ያለ ብሬልና በአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ጉዳተኞች ደግሞ ያለተስማሚ መግቢያና መውጫ መንገድ ይማሩ ቢባል እንኳን ውጤታማ መሆን አይችሉም ብለዋል።

እስካሁን በአብዛኛው መስማት የተሳናቸው በጥቁር ሰሌዳ የተፃፈውን ገልብጠው ከመውጣት፣ ዓይነስውራን ደግሞ የሚባለውን ሰምተው ከመውጣት የዘለለ ንቁ የትምህርት ተሳትፎ እንደማያደረጉ አቶ አባይነህ ተናግረዋል።

የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ህፃናትም በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ጥቂቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።

በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ችግሮቹን ከመሠረቱ በመለወጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተደራሽነት ይረጋገጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል ።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ማስተባበሪያ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ሁሉም አካል ጉዳተኛ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንደማይመጡና የመጡትንም ቢሆን ምቹ የትምህርት አካባቢ እንዳልተፈጠረላቸው በመግለጸ የቅሬታውን ተገቢነት አረጋግጠዋል።

በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት ላይ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

ለፍኖተ ካርታው ግብአት የሚሆን ሃሳብ ለማሰባሰብም አገራዊና ክልላዊ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፣ የትምህርትና የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊዎችና  ባለድርሻ አካላት ያካተተ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ መካሄዱን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከ17 ሚሊዮን የሚበልጡ አካል ጉዳተኛ ወገኖች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም