አንጋፋ ፖለቲከኞች ልምዳቸውን በማካፈል በወጣቶች መተካት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
አንጋፋ ፖለቲከኞች ልምዳቸውን በማካፈል በወጣቶች መተካት አለባቸው
አዲስ አበባ የካቲት 07/2011 አንጋፋ ፖለቲከኞች ወደ ስልጣን ከወጡ በኋላ አንለቅም የሚሉትን ባህል በማስወገድ ወጣቶችን መተካት እንዳለባቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
የሀገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ ከሚወስኑት አብዛኛው ድርሻ ያለውን ወጣት ወደ አመራርነት ለማምጣት የፖለቲካ ድርጅቶች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ እንደገለጹት ኢህአዴግ ራሱን በአዲስ የወጣት ጉልበት እየተካ ነው፡፡
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጉባኤዎቻቸውን ሲያካሂዱ አብዛኛው ተሳታፊ ወጣት እንደነበረና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎቻቸው እስከ 90 በመቶ ወጣቶች መሆናቸውን አቶ ፈቃዱ አስታውሰዋል፡፡
የወጣቶች ሊግ በቅርቡ ጉባኤውን ሲያካሂድ አቅም ያላቸውን ወጣቶች በማሳተፍ ወደ አመራርነት በማምጣት የወጣቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢህአዴግ የወጣት አደረጃጀቶች በድርጅቱ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ ለወጣቶች ጥቅም የሚከራከሩ፣ የወጣቶች ጥያቄ የሚያነሱ እና ተፅእኖ ፈጣሪ ወጣቶች ወደ ራሳቸው በመሳብ አብዛኛው ወጣት የሚወክሉበት ሁኔታ በሚፈለገው መልኩ አለመፈጠሩንም ነው ሃላፊው የተናገሩት።
በዚህም የወጣቶች ሊግ የነበረውን ችግር በመለየት ወደፊት ሊያሰራው የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ዝርዝር ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በለውጡ ወቅት ለራሳቸው የተለያየ ስያሜ ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶች ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር እንዲሁም ለውጡን ለማስቀጠል እንዲችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች እንደተሰጠም ነው አቶ ፍቃዱ የጠቀሱት።
በኦሮሚያ ከክልል እስከ ወረዳ የትግል አግባብ ምን መሆን አለበት ፣ለውጡ መቀጠል የሚቻልበት፣ የወጣት ሚና በአገር ግንባታ ውስጥ ምን መሆን እንዳለበትና የወጣት መብት እና ግዴታ ምን እንደሆኑ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስልጠናዎች መሰጠቱን ለአብነት አንስተዋል።
ማንኛውም ልማትም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለ ወጣት አይታሰብም ያሉት አቶ ፍቃዱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ በስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ አመራሮች መተካካትን መልመድ አለባቸው ብለዋለ።
ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የምትፈለገውን የፖለቲካ እሳቤ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወጣት አመራሮችን ወደፊት እያመጣ እንደሆነ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
“የ1960ዎቹ ትውልድን ጡረታ ማስወጣት የሚችል ኃይል ከወጣቶችም ጭምር መፈጠር አለበት” ያሉት ደግሞ የመድረክ እና ኢፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው ፡፡
ወጣቶች ላለፉት 27 ዓመታት ከቆየው አፈና ለመውጣት ባደረጉት እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣታቸውን ያነሱት ፕሮፌሰር መረራ፤ የፖለቲካ እስረኞች የተፈቱትም በወጣቶች ንቅናቄ ነው ብለዋል።
መድረክ ለወጣቶች በሩን ክፍት አድርጓል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ አሁን በሀገሪቱ በመጣው ለውጥ የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑንና በእድሜ ከገፉት ፖለቲከኞችም ልምድና እውቀትን ሊያገኙ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የአዲስ አበባ አደራጅ ግብረሃይልና የሰሜን ሸዋ አደረጃጀት ተወካይ ወይዘሪት ከውሰር ኢድሪስ በበኩሏ ንቅናቄው የወጣቶች እየሆነ መምጣቱን ገልጻ ለአብነትም የአዲስ አበባ የአባላት አደራጅ ጊዜያዊ ግብረሃይል ሁሉም ወጣቶች ናቸው ብላለች።
ወይዘሪት ከውሰር “የፖለቲካ አመራሩ የ1960ዎቹ ትውልድ ነው የሚለው ገጽታው ተቀርፎ በወጣቶች እየተተካ እንዲሄድ ወጣቶች ወደ መድረኩ ብቅ ብቅ ማለት አለባቸው” ስትል አስታውቃለች።
“ባቋቋምናቸው 23 የምርጫ ክልል ውስጥ 90 በመቶዎቹ ወጣቶች ናቸው፣ የንቅናቄው ፖሊሲ በዜግነት ፖለቲካና በማህበራዊ ፍትህ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ አቅም ያላቸው ወጣቶች በሩ ክፍት እንዲሆንላቸው አድርጓል” በማለትም ሃላፊዋ ገልጻለች።
አንጋፋ ፖለቲከኞች ወደ ስልጣን ከወጡ በኋላ አንለቅም የሚሉትን ባህል በማስወገድ ለወጣቶች ልምድ በማካፈል ወደ ፖለቲካ አመራርነት ተቀላቅለው ተተኪ በመሆን የሀገር ጉዳይ ይመለከተናል በማለት እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ብላለች።
ወጣቶች ለራሳቸው የሚሆናቸውን ውሳኔ በፖለቲካው ውስጥ ገብተው ካልወሰኑ ሌሎች የሚወስኑላቸውን ለመቀበል ስለሚገደዱ በፖለቲካው በቀጥታ በመሳተፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ወሳኝ መሆን እንዳለባቸው ነው ወይዘሪት ከውሰር የገለፀችው።