መከላከያ ለአገራዊ ለውጡ መሳካት የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ነው - ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ለአገራዊ ለውጡ መሳካት የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ነው - ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም
አዲስ አበባ የካቲት 7/2011 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአገራዊ ለውጡ መሳካት የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሆነ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን ተናገሩ።
"ህገ መንግስታዊ ታማኝነታችንንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል ዛሬ በተከበረው 7ኛው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን ላይ ነው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የተናገሩት።
ጀነራሉ እንዳሉት የመከላከያ ሰራዊቱ ለተጀመረው አገራዊ ለውጥ ስኬት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት በመወጣት ላይ ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ የአገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል ያሉት ጀነራል ሰዓረ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው ሪፎርም ሰራዊቱን ዘመናዊና በሙያ የተካነ አድርጎ የመገንባት ተግባር እየተከናወነ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
ጀነራል ሰዓረ እንዳሉት ተቋሙ ህገ-መንግስታዊ ተልኮውን በመወጣት የአገሪቱን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት ይወጣ ዘንድ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ለማብቃት የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አደራጃጀቱም የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትና አዳዲስ የሰው ኃይል ለማካካተት በሚያስችል መንገድ ለመገንባት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"ሰራዊታችን በስራ ላይ እያለ ኑሮ የሚሻሻልበት፣ በክብር ከተሰናበት በኋላም የሚቋቋምበት አሰራር ለመዘርጋት በዝግጅት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በመጠበቅእና በማንኛውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆን ኃላፊነቱን ይወጣል ሲሉም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቡ፣ የተለያዩ የጸጥታ አካላት እና መንግስት ቁርጠኝነትና የክልሎች ድጋፍ ለሰራዊቱ ውጤታማነት አስተዋዕጾ ማድርጉን ገለጸዋል።
ሰራዊቱ በክልሎች ጥሪ እየተደረገለት በየአካባቢው ሰላም ለማስፍን ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካላት የሚካሄድበት የስም ማጥፋት ተግባር ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
7