የኢትዮጵያና ኬንያ የንግድ ልውውጥ በአራት እጥፍ አድጓል - የአፍሪካ ልማት ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኬንያ የንግድ ልውውጥ በአራት እጥፍ አድጓል - የአፍሪካ ልማት ባንክ
አዲስ አበባ የካቲት 7/2011በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የተገነባው መንገድ የሁለቱን አገሮች የንግድ ልውውጥ በአራት እጥፍ እንዲጨምር ማስቻሉን የአፍሪካ ልማት ባንክ ገለጸ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና ለኢዜአ እንደተናገሩት ባንኩ በኢትዮጵያ የትራንስፖርትና የኃይል መሰረተ-ልማቶችን ለማገዝ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
አዲስ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪዎችን ለመገንባት የሚያስችል ፋይናንስ ድጋፍ እያቀረበ እንደሆኑና በዚህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማፋጠን አየሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚዘልቀውን የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ባንኩ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በመቻሉና ልማቱ እውን በመሆኑ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የመንገዱ መገንባት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን የንግድ ልውውጥ በአራት አጥፍ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ልማት፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት፣ የሃዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክን ከጂቡቲ ጋር በመሰረተ-ልማት እንዲተሳሰር እንዲሁም ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከውኃ የአሌሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የምታደርግው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ በዚህም ረገድ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ብድር በአግባቡ አየተጠቀመች መሆኑን ገልጸው ምጣኔ ኃብቷን ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
በተለይም ደግሞ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ጥሬ እቃ እሴት እንዲጨምር ለማድረግም ጭምር።
የግሉ ዘርፍ ለምጣኔ ኃብት እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እንዲጎለብት በተለይም ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ባንኩ የኢትዮጵያ የገጠር ምጣኔ ኃብት መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ ትርፋማ እንዲሆን ለማስቻል ድጋፉን እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የምጣኔ ኃብት ሥራዎች ባንኩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።