ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት 106 ሺህ ከረጢት ደም ሰበሰበ

146

አዲስአበባ  የካቲት 6/2011 ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ 106 ሺህ ከረጢት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መሰብሰቡን አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 38 ሺህ ከረጢት ደም ከበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች በማግኘት የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት ችሏል። 

የዕቅድ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 ሺህ ከረጢት ደም ብልጫ አለው።

የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን ኃይሉ እንዳሉት የኀብረተሰቡ በፈቃደኝነት ደም የመለገስ ልምድ እያደገ በመምጣቱ በግማሽ ዓመት 90 በመቶ የዕቅድ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል። 

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፈቃደኝነት የደም ልገሳ ካደረጉ በኋላ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቁጥር እንደጨመረም ገልጸዋል።

አንድ ሰው የሚለግሰው ደም የሦስት ሰዎችን ህይወት ማዳን እንደሚቻል የገለጹት ዶክተር ሄለን ኀብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርገው ይገባልም ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር ሄለን ገለጻ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 65 ዓመት ድረስ ያሉ ሰዎች ደም ቢለግሱ የዜጎችን ህይወት ከመታደግ ባሻገር ለራሳቸውም ጤንነት ጠቃሚ ነው።

አንድ ሰው ደም በሚለግስበት ወቅት አሮጌው የደም ህዋስ በአዲስ የሚተካ በመሆኑ ከደም ጋር በተያያዘ ከሚፈጠር ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት መዳን እንደሚቻልም አስረድተዋል።     

ጄ ኤሰ አይ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት መስራት የጀመረበትን 25ኛ ዓመት ዛሬ ደም በመለገስ አክብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም