በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራ ተጀመረ

74
ሚዛን ግንቦት 21/2010 በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ የተስተጓጎለው የመማር ማስተማር ስራ  ዛሬ ሙሉ በመሉ መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አስታወቁ፡፡ በሚዛን አማን ከተማና በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ረብሻ ለመፍታት በተደረገው ጥረት አካባቢውን ወደ ቀድሞ ሰላም መመለስ ተችሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል ለኢዜአ እንደገለጹት በችግሩ ዙሪያ ከተማሪዎች ጋር ተወያይተው መግባባት ላይ በመድረሳቸው  ለአንድ ሣምንት ያህል ተቋርጦ የቆየው  የመማር ማስተማር ስራ ዛሬ በተሟላ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡ በውይይቱ ወቅት ችግር ካለም በህጋዊ አግባብ መጠየቅ እንጂ በመረበሽ ትምህርት እንዲቋረጥና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ተገቢ እንዳልሆነ ግንዛቤ መወሰዱንም አመልክተዋል፡፡ የተማሪዎች የምግብ አገልግሎትን ጨምሮ ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደራዊ ስራ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሷል፡፡ " በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል "ብለዋል፡፡ ድርጊቱ ሁሉንም ተማሪዎች የሚወክል ሳይሆን በተወሰኑ ተማሪዎች የተፈጸመ መሆኑን ገልጸው በድርጊቱ ተሳታፊ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ ሰባት ተማሪዎችና ሦስት የአስተዳደር ሠራተኞች በህግ አስከባሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ " በቀጣይ የሰላም ስጋቶችን ለይቶ  ፈጣን የመፍትሔ እርምጃ በመውሰድ ተመሳሳይ  ችግር እንዳይከሰት በትኩረት ይሰራልም "ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው  የአንደኛ ዓመት የእንስሳት ሳይንስ ተማሪ አወቀ ፈለቀ በሰጠው አስተያየት " በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር የለም " ብሏል፡፡ በወቅቱ በነበረው ረብሻ ምክንያት ትምህርት በመስተጓጎሉና ንብረት ላይ ጉዳት በመድረሱ ማዘኑን ገልጾ ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረጉ አካላት ተለይተው ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ የሁለተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪው  ሸጋው አዳነ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ሠላማዊ ሁኔታ በመፈጠሩ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን ተናግሯል፡፡ " ተማሪዎች እውቀት ለመቅሰም እስከመጣን ድረስ ትኩረታችን ትምህርት ላይ ብቻ መሆን አለበት "ብሏል፡፡ ተማሪ ሸጋው ጥያቄ ሲኖርም በሰለጠነ አካሄድ የሚመለከተውን አካል መጠየቅ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ በሚዛን አማን ከተማ ተስተጎጉሎ የቆየው የንግድ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው ተዘዋውሮ ማረጋገጡን ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም