ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባየካቲት 6/2011 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው በዚሁ ውይይት ላይ የኮሚቴው የስራ እንቀሰቃሴዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል።
በውይይቱ ወቅት ኮሚቴው በስራዎቹ ያስመዘገባቸው ውጤቶችም ተገምግመዋል።
ኮሚቴው የሙስሊሙን አንድነት ለማጠናከርና ሰላም ለማረጋገጥ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አጽንኦት ተሰጥቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኮሚቴው ያስመዘገባቸውን ውጤቶች እንዲያጠናክር አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን፤ እርሳቸውም የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ወራት በፊት ከኮሚቴው ጋር በነበራቸው ውይይት የኮሚቴውን የግጭት አፈታት ሂደትና የተገኙ ውጤቶችን መገምገማቸው ይታወሳል።
በወቅቱም የተመዘገበውን ለውጥ በመረዳት በተለይም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ አንድነትን የሚያጠናክር ተቋም መመስረቱን አድንቀውም ነበር።
በመሆኑም መግባባቶችን ለማጠናከር እንዲሁም ለማደናቀፍ የሚሰሩ ማናቸውንም እንቅፋቶች በመከላከል የመንግስት ድጋፍ እንደሚቀጥል መግለፃቸውም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ያዋቀራቸዉ አራት ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዳሉት ይታወቃል።