በግል ጤና ተቋማት ላይ የሚታውን ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በግል ጤና ተቋማት ላይ የሚታውን ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 6/2011 በግል የጤና ተቋማት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ተባለ።
የጤና ሚኒስትር ከዓለም ባንክ እና ግሎባል ፋይናንስ ጋር በመተባበር የግልና የመንግስት ጤና ተቋማት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የአቅም ማጎልበቻ አውደ ጥናት አዘጋጅቷል ።
የኢትዮጵያ የግል ጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ ''በግል ጤና ተቋማት ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ ግልጽ የሆነ የፖሊሲ ድጋፍ ያስፈልጋል'' ብለዋል።
ዶክተር ማርቆስ እንደተናገሩት፤ እንደሌሎች የግል የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለግል የጤና ተቋማት ድጋፍ አይደረግም።
የጤና ባለሙያ እጥረት፣ የፋይናስ ችግር፣ ከሊዝ ነጻ መሬት አለማግኘት፣ የመስሪያ እቃዎችንከቀረጥ ነጻ ያለማስገባት እና የባንክ አገልግሎት አለመሻሻል ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም በጤናው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችን የሚደግፍና የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው የፖሊሲ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የግሉ የጤና ዘርፍ ከመንግስት ጋር ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ በመተጋገዝ ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የኦፕሬሽናል ጀኔራል ዳይሬክተር ዶክተር የቆየሰው ወርቁ እንዳሉት፤ ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የግሉም ሆነ የመንግስት የጤና ተቋማት ተባብረው መስራት አለባቸው።
''ጤናማና ምርታማ ማህበረሰብ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች ማሰልጠንና ጤና ጣቢያዎችን መገንባት ብቻውን የሚፈለገውን ዓላማ ለማሳካት አያስችልም'' ብለዋል።
የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርበው እንዲሰሩ መንግስት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ለግል የጤና አገልግሎት አቅራቢዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ችግሮችን በአግባቡ መለየትና ተገቢውን መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ሚኒስቴሩ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ በጤና አገልግሎት የግል ዘርፉ እያደገ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።