በመቱ ከተማ ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመቱ ከተማ ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
መቱ የካቲት 6/2011 በመቱ ከተማ ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ቡልቻ ታምሩ ለአዜአ እንዳሉት በዚህ ዓመት ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ያተኮሩት በመንገድና በኤሌክትሪክ ዝርጋታ ሥራ ላይ ነው።
በበጀት ዓመቱ 18 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ የመንገድ ግንባታ ሥራ ለማካሄድ በታቀደው መሰረት እስካሁን የስምንት ኪሎ ሜትር ጠጠር ማልበስ ሥራ ተጠናቆ መንገዱ ለትራፊክ እንቅስቃሴ ክፍት ሆኗል።
ቀሪውን የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው በተለያዩ አቅጣጫዎች የሁለት ኪሎ ሜትር ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሥራ በቅርቡ መጀመሩንም አቶ ቡልቻ ተናግረዋል።
የሦስት ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ ሥራ በአሁኑ ወቅት በመፋጠን ላይ ሲሆን ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ 116 የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ፖል ተከላና መስመር ዝርጋታ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ምክትል ከንቲባው አቶ ቡልቻ እንዳሉት እስካሁን ድረስ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።
"ሁሉም የመሰረተ ልማት ስራዎች ሲጠናቀቁ የነዋሪውን የረጅም ጊዜ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በተሻለ መፍታት ይቻላል" ብለዋል።
በመቱ ከተማ ቀበሌ 03 የሚኖሩት ወይዘሮ ጫልቱ አሰፋ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በከተማዋ ዘንድሮ እየተካሄዱ ያሉ የመንገድና የመብራት ዝርጋታ ሥራዎች የከተማውን ገጽታ እየቀየሩ ስለመምጣታቸው መታዘባቸውን ገልጸዋል።
" ከተማዋን ለኢንቨስትምንትና ለኑሮ ይበልጥ አመቺ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሊስፋፋ ይገባል" ያሉት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ አቶ ጀማል አብዱ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ የልማት ሥራዎች ተጀምረው የሚቆሙበት ሁኔታ ስለነበር ህብረተሰቡ ቅሬታውን ሲያሰማ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ጊዜያት ከህብረተሰቡ ለተነሱ የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ መሰጠት በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጀማል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ እየታየ ያለው የልማት መነቃቃት እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።