"ካለፉት 27 ዓመታት ጉዞ ጥሩውን በማጠናከር፣ መጥፎውን በመተው ለላቀ አገራዊ ድል መትጋት ይገባል" -ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ

14
አዲስ አበባ ግንቦት 20/9/2010 ካለፉት 27 ዓመታት ጉዞ ጥሩውን በማጠናከር፣ መጥፎውን በመተው ለላቀ አገራዊ ድል መትጋት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ። 27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል የመዝጊያ ስነ ስርዓት "የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞኪራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ በሻራተን አዲስ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፤ "የዘንድሮው የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር በፈጣንና መሰረተ ሰፊ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ሆነን ነው" ብለዋል። "ዕለቱም የኢትዮጵያውያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጭቆናን ለማስወገድ የከፈሉት መራራ የትጥቅ ትግል በድል የተደመደመበት፤ በምትኩም ብዝሃነትን ያከበረ የዴሞኪራሲያዊ አንድነት ስርዓት መሰረት የተጣለበት በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ቦታ አለው" ብለዋል። ያለፉት 27 ዓመታት እንደ አገርና እንደ ህዝብ ህልውናችንን ሲፈታተኑ የነበሩ በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙን የነበሩ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ምንም እንኳን ያጋጠሙን ችግሮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማደብዘዝ ባይችሉም፤ "የአገሪቷን ሰላምና አንድነት እስከ ማናጋት የደረሱበት ሂደት የሚታወስ ነው" ብለዋል። በመሆኑም ዕለቱን ስናከብር በትናንትናው የትግላችን መንገድ ላይ ሆነን በተገኘው ድል ሳንኩራራ ያጋጠሙን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላይ አተኩረን ለመስራት ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ባጠቃላይ ካለፉት 27 ዓመታት ጉዞ ጥሩውን በማጠናከር፣ መጥፎውን በመተው ለላቀ አገራዊ ድል መትጋት እንደሚገባ ነው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ያሳሰቡት። በበዓሉም፤ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶችና የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም