ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድበትን መንገድ ሉክሰንበርግ አደነቀች

አዲስ አበባ የካቲት 6/2011ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን የሉክሰንበርግ የውጭ፣ የአውሮጳና ስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ጂን አሰልቦርን ተናገሩ።

ሉክሰንበርግ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ጥሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሉክሰንበርግ የውጭ፣ የአውሮፓና ስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትሩን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ችግርን በመሸሽ የፈለሱ የጎረቤት አገር ዜጎችን በመቀበል ረገድ ምሳሌ የምትሆን አገር ናት።

በቆይታቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ የስደተኛ ካምፖችን መጎብኘታቸውንም ጠቁመዋል።

የስደተኞች ጉዳይ በአውሮፓ ትልቅ የመከራከሪያ ርዕስ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጎረቤት አገር ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና ሉክሰንበርግ ድርብ ታክስን ለማስቀረት ያደረጉት ስምምነት በጥሩ መንገድ እንደሚገኝም አውስተዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአገራቸው የካርጎ ካምፓኒዎች መኖር ስላለበት ትብብር ከፕሬዝዳንቷ ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።

ሉክሰንበርግ በኢትዮጵያ የፋይናስ ስርዓቱ ላይ ማድረግ ስላለባት እገዛ ፍሬያማ ምክክር መደረጉንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈጠሩት ሰላማዊ ግንኙነት ሉክሰንበርግን እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ አገራቸው ይህ መልካም ጅምር ወደ ላቀ ትብብር እንዲሸጋገር እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት ያላቸው አገራት ናቸው።

ሉክሰምበርግ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በ2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የከፈተች ሲሆን በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራስልስ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አገሪቷ ከሉክሰምበርግ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይሸፍናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም