ለ8ኛው የከተሞች ፎረም ጅግጅጋ እንግዶቿን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች

104

ጅግጅጋ የካቲት 6/2011 በመጪው ቅዳሜ በጅግጅጋ ከተማ ለሚካሄደው ስምንተኛው ሀገር አቀፍ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የፎረሙ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።


የፎረሙ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የሚያርፉበት ስፍራዎችና አንድ ሺህ ሁለት መቶ የእንግዶ ማረፊያ ክፍሎች በከተማው በሚገኙ ሆቴሎች መዘጋጀታቸውም ታውቋል።

በበዓሉ ማስተባበሪያ ክልላዊ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰመተር መሀመድ እንደገለጹት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ጅግጅጋ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት፣ ጅግጅጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና የዶክተር አብዲመጂድ ሁሴን የመምህራን ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ተጨማሪ ማረፊያዎችን አዘጋጅተዋል።


በከተማው ስታዲየም የሚዘጋጀው የመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ደማቅ ስፖርታዊ ትይዕንት የሚያሳዩ ወጣቶችም ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።


ከተሞች ኤግዚብሽን የሚያሰዩበት ቦታ ዝግጅትና የንግድ ባዛር የሚካሄድባቸው ሥፍራዎች የድንኳን ተከላና ሌሎች ዝግጅቶች በሙሉ መጠናቀቃቸውንም የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ተመልክቷል።


ከፎረሙ ጋር ተያይዞ በስልሳ ሚሊዮን ብር በከተማው የተጀምሩ ስድስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ዳር እና ዳር አረንጓዴ የማልበስና አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ጥርጊያ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታም ተጠናቋል።


እንዲሁም ሁለት ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ የመገንባት ስራ በአብዛኛው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የከተማ አገልግሎት የመንገድ ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂኒየር አብዲቃድር መሀመድ ተናግረዋል።


መድረኩ በከተሞች መካከል ተቀራራቢ ልማትና እድገት በማምጣት ከተሞችን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማዕከል የማድረግ ግብ እንዳለውም ገልጸዋል።


ባለፈው ዓመት በጎንደር ከተማ በተካሄደው ሰባተኛ ፎረም ላይ ስድስት የክልሉ ከተሞች መሳተፋቸውን አስታውሰው ዘንድሮ በጅግጅጋ በሚካደው 8ኛው የከተሞች ፎረም ላይ 19 የክልሉ ከተሞች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

 
በመድረኩ ላይ 165 ከተሞች እና ከአስር ሺህ በላይ እንግዶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።


ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ እስከ የካቲት 14/2011 ዓ.ም. የሚከበረው 8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" የሚል መሪ ሃሳብ እንዳለው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም