የኢትዮጵያ ሕክምና ማሕበር ዓመታዊ የሕክምና ጉባዔውንና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕክምና ማሕበር ዓመታዊ የሕክምና ጉባዔውንና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ያካሂዳል
አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 የኢትዮጵያ ሕክምና ማሕበር 55ኛውን ዓመታዊ የሕክምና ጉባዔውንና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ ነው።
ጉባዔና አውደ ርዕዩ ከየካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ "ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ አዳራሽ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል።
በዝግጅቱ የጤና ሚኒስትሩን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች፣ በጤና ዘርፍ የተሰማሩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ አጋር ድርጅቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ አምራቾችና አስመጪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የህክምናው ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ፣ ያሉበት ችግሮችና የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የጋራ ዓላማቸው ባደረጉ አካላት ውይይት እንደሚካሄድባቸው የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት መኮንን ገልፀዋል።
የደም ልገሳ፣ የፓናል ውይይቶች፣ ከ40 በላይ የጥናትና ምርምር ጽሁፎች በመርሃ ግብሩየተካተቱ ሲሆን አምስት ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ሩጫም ይካሄዳል።
ማህበሩ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያከናውን ሲሆን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እንዲጠበቅ፣ የህክምና ባለሙያዎች ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና በሥነ ምግባር የታነፀ አገልግሎት ለማህበረሰቡ እንዲሰጡ ሥልጠናዎችን ይሠጣል።
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በ1954 ዓ.ም በ100 አባላት የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅትዘጠኝ ቅርጫፍ ፅህፈት ቤቶችና ከሶስት ሺህ በላይ አባላት አሉት።
ማህበሩ በቆይታው ከ1 ሺህ 790 በላይ በህክምና ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎችንም ለህትመት አብቅቷል።