አርባ ምንጭ ከነማ የወልዲያ አቻውን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
አርባ ምንጭ ከነማ የወልዲያ አቻውን አሸነፈ
አርባምንጭ ግንቦት 20/2010 በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አርባ ምንጭ ከነማ የወልዲያ አቻውን በሜዳው አስተናግዶ በሰፊ ጎል አሸነፈ፡፡ ወራጅ ቀጠና ውስጥ በሆኑት ሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ ባለሜዳው አርባ ምንጭ አምስት ለዜሮ በሆነ ውጤት ነው ማሸነፍ የቻለው፡፡ ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የመሩት ሲሆን በማጥቃት ላይ በተመሰረተው ጨዋታ አርባ ምንጭ ከነማ የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው አለልኝ አዘነ በ40ኛው ደቂቃ በ20 ሜትር ላይ ባገኘው የቅጣት ምት ነው፡፡ ከእረፍት መልስ በ52ኛ፣ በ70ኛ፣ እና በ82ኛው ደቂቃዎች በአጥቂ ክፍል የተሰለፈው ተመስገን ካስትሮ በተከታታይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ ሠርቷል ፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ደግሞ በረከት አዲሱ የማሳረግያውን ጎል ለአርባ ምንጭ አስቆጥሯል ፡፡ ከጨዋታው መልስ የአርባምንጭ ከነማ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ጃክሰን ፊጣ " ካለንበት ደረጃ አንፃር ወሳኙን ጨዋታ በድል መወጣታችን ለክለቡና ደጋፊዎች ደስታን ያጎናጸፈ ነበር" ብለዋል ፡፡ የድሉ ምስጥር የተጫዋቾች ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዲሁም በተደረገው ተጫዋቾችን የማሸጋሸግ ሥራ በጥንቃቄ በመሥራታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል ፡፡ "በዚሁ ተነሳሽነት ቀጣይ ሳምንት ከደደቢት ጋር አዲስ አበባ ላይ የምኖረንን ጨዋታ በድል ለመወጣትም ጠንክረን እንሠራለን " ነው ያሉት ፡፡ የወልዲያ አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራዉ በበኩላቸው "አርባ ምንጮች ድሉ ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡ "በቀጣይ የክለቡን መሠረታዊ ችግር በማስተካከል ድሎችን አስመዝግበን ክለቡ በሊጉ እንዲቆይ ጠንክረን እንሰራለን " ሲሉም ጠቅሰዋል ፡፡