ምርታማነት ለማጎልበት የኢንዱስቱሪ ሰላም ማስፈን ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ምርታማነት ለማጎልበት የኢንዱስቱሪ ሰላም ማስፈን ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ
መቀሌ ግንቦት 20/2010 ምርታማነት ለማጎልበትና የኢንዱስቱሪ ሰላም ለማስፈን በአሰሪዎችና ሰራተኞች የሚነሱ አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ በአሰሪዎችና ሰራተኞች መካከል በሚፈጠሩ ክርክሮች አፈታት ዙሪያ የትግራይ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል፡፡ ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የትራንስ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስክያጅ አቶ መውጫ ወልዱ እንዳሉት የአሰሪዎችና ሰራተኞች መብትና ጥቅም ማስከበር ከሁሉም በላይ ለኢንዱስትሪ ሰላም መረጋገጥ የጎላ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የኢንዱስትሪ ሰላም መረጋገጥ ደግሞ የሰራተኞችን የተደራጀ አቅም በመጠቀም ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ምርታማነትን ለማጎልበት በአሰሪዎችና ሰራተኞች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአቢሲንያ ብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በሪሁ መኮነን በበኩላቸው ''ሰራተኞች በስራ ቦታ እንዲደራጁ ማበረታታት የሰራተኛውንም ሆነ የአሰሪውን መብት ከማስከበር ባለፈ የሚፈልጉትን ጉዳይ ህግን መሠረት አድርገው እንዲጠይቁ ያግዛል'' ብለዋል፡፡ ይህም አገራዊ እድገት ለማምጣት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። የሰራተኛውና አሰሪዎች መካከል አልፎ አልፎ የሚታዩ ክፍተቶች ለመሙላት እንዲህ አይነት የውይይት መድረኮች ወሳኝ ናቸው ያሉት ደግሞ የትግራይ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ልኡል ክንፈ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ከየት ወዴት፣ ግንቦት 20 ለባለሃብቱ ያለው ትሩፋትና ማህበራዊ ምክክር ለኢንዱስትሪ ሰላምና ምርታማነት ለማጎልበት ያለው ፋይዳ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል። ከአገር አቀፉ የአሰሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የአንድ ቀን የውይይት መድረክ በርካታ የኢንዱስትሪ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡