ከህዳሴው ግድብ መዘግየትና ኃብት ብክነት ጋር ተያይዞ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን እምነት ማጣት መቀልበሰ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ከህዳሴው ግድብ መዘግየትና ኃብት ብክነት ጋር ተያይዞ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን እምነት ማጣት መቀልበሰ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ ጋር ተያይዞ በሚስተዋለው መዘግየትና የኃብት ብክነት ምክንያት በህዝብ ዘንድ ሊፈጠር የሚችለውን የእምነት ማጣትና የተሳትፎ መቀዛቀዝ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን አንዳለባቸው ተገለፀ።
የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ሲካሄድ የጉባኤው ተሳታፊዎች እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ግድቡ ያለበትን ደረጃ፣ የገጠሙትን የተለያዩ ፈተናዎችና ወደፊት ሊወሰዱ የታሰቡትን እርምጃዎች በተመለከተ አውነተኛና ግልፅ መረጃ ለህዝቡ ማሰራጨት ይገባል።
ይህን ለማከናወንም ቢቻል የመንግስት አካላትን ጨምሮ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸውንና ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ቡድን በመላው አገሪቱ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታ ማስወገድ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
'የግደቡ ሥራ ቆሟል' የሚለውን የሀሰት ዜና ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ከህዳሴው ግድብ ሥራ ጋር በተያያዘ ያለው እይታ ተቀይሯልም ተብሏል።
ይህን በማድረግ የተቀዛቀዘውን የህዝብ አመኔታና ተሳትፎ መልሶ ለማምጣት ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ለህዝቡ ትክክለኛውን መረጃ በየጊዜ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
ህዝቡ እውነቱን ከተረዳ ለተፈፀሙት ጥፋቶች ይቅር የሚል ቅን ከመሆኑም በላይ የህዳሴውን ግድብ ታላቅ አገራዊ ፋይዳ ያለውና የታሪኩ አካል አድርጎ ይመለከተዋል፤ ምንም ይሁን ምን ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የሚከፈለውን ሁሉ የመክፈል ፍላጎት አለውም ነው የተባለው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ህዝቡ በግድቡ ላይ አመኔታ ቢያጣ አይፈረድበትም ብለዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም የመንግስት ትኩረት ቦንድ መሰብሰብ ሳይሆን በቅድሚያ የህዝቡን አምኔታ ወደ ነበረበት በመመለስ መጠገን እንደሆነም አብራርተዋል።
የህዳሴው ግደብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንዳሉት ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ በህዝቡ ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው እምነት ማጣትና ተሳትፎ መቀዛቀዝ በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መጥቷል።
ምንም እንኳ ህዝቡ በፕሮጀከቱ መዘግየትና ሌሎች ችግሮች ሳቢያ የተቆጣ ቢሆንም ባለፉት ስድሰት ወራት ብቻ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የቦንድ ግዢን ጨምሮ ህዝቡ በጠቅላላው ባለፉት ዓመታት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።