ዩኒሴፍ ለተንቀሳቃሽ ህክምና 30 ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒሴፍ ለተንቀሳቃሽ ህክምና 30 ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ የካቲት4/2011 የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የህጻናት አድን ድርጅት(unicef) ከጀርመን መንግስትጋር ለተንቀሳቃሽ ህክምና 30 ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊያደርጉ ነው።
ተሽከርካሪዎቹ ለአፋርና ሱማሌ ክልሎች የሚውሉ ሲሆን ነገ ለጤና ሚኒስቴር እንደሚያስረክቡ ነው የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የህጻናት አድን ድርጅት የገለጸው።
በድጋፍ ከሚሰጡት 30 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 11 ለአፋርና 19 ለሱማሌ ክልል ሲሆን ድጋፉም በጤና ሚኒስቴር በኩል ይተላለፋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት፣ ስርዓት እንዲሁም አስቸኳይ የህክምና አገልግሎትን ለማዳረስ እየሰራ ይገኛል።
ሆኖም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩና ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት እንደ ልብ አያገኙም።
ይህንን ችግር ለመፍታትም መንግስት ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎትን እንደ አማራጭ እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን የሚደረገው የመኪና ድጋፍም ተንቀሳቅሶ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ተብሏል።
በአፋርና ሱማሌ ክልል መንግስት ለሚያከናውነው የስርዓተ ምግብ ተግባርም ተሽከርካሪዎቹ እንደሚያገለግሉ ተገልጿል።
ድጋፉ የኢትዮጵያ መንግስት በስርአተ ምግብ ላይ እየሰራ ያለውን ተግባር በታዳጊ ክልሎችም በተመሳሳይ እንዲሄድ ለማገዝም ነው ተብሏል።