ቀጥታ፡

በአፍሪካ ግጭት በነበረባቸው አገሮች መሻሻል መታየቱን የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ገለጸ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 በአፍሪካ ግጭት በነበረባቸው አገሮች መሻሻል መታየቱን  የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ገለጸ።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ኢስማኤል ቸርጎይ በአህጉሩ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው በሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጊኒ ቢሳዎና በሰሃል አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላምና ጸጥታ ሰፍኗል።

በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ግን አስቸጋሪ በመሆኑ በትብብር መስራት አንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በሊቢያ ለዓመታት የቆየውን ችግር ለመፍታት ጥረት መጀመሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በጉዳዩ ላይ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነም አመልክተዋል።

በአካባቢው ያሉት ሚሊሻዎች፣ የታጠቁ ቡድኖችና የውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት ሰላም ያጣችው ሊቢያ ሰላም እንድታገኝ ሊቢያዊያን ችግራቸውን በራሳቸው እንዲፈቱት ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሊቢያ ያለው ቀውስ በአካባቢው አገሮች ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን ተናግረው በቅርቡ በቻድ የተፈጸመው ጥቃት የዚህ ማሳያ እንደሆነም አንስተዋል።

በሶማሊያ የአሸባሪ ኃይሎችን ከመዋጋት ጎን ለጎን ጸጥታውን የማስከበር ሃላፊነቱን ለአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ለማስረከብ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በጊኒ ቢሳዎ በሚያዝያ ወር የሚካሄደውን ምርጫ መሰረት አድርጎ ችግር እንዳይከሰትና በተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል አለመግባባት እንዳይፈጠር ከወዲሁ የፊት ለፊት ድርድር ለሁለት ሳምንት ተካሂዶ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

በሳሃል አካባቢዎች የሚታየውን የሽብር እንቅስቃሴዎች ለመግታትም ከአካባቢው አገሮች  ጋር በትብብር በመስራት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን መመልከት እንደተቻለም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም