ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ማራዘሚያ ጊዜ ሊኖር አይገባም...ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ  የካቲት 4/2011 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተያዘው የጊዜ መርሃ-ግብር ለማጠናቀቅ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት የነበረው ግድቡ ሳይጠናቀቅ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል።

በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አማካኝነት መሰራት የነበረበት የግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካልና ተያያዥ ተግባራት አፈፃፀም በመጓተቱ ስራውን በተያዘው ጊዜ ማጠናቀቅ ያልተቻለው።

በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ አራት ዓመታት አስፈልጓል። 

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ፕሮጀክቱን በተያዘው አራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በጥራትና በብቃት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ክትትል ያደርጋል ብለዋል የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለፁት ዛሬ የምክር ቤቱ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው።

እርሳቸው እንዳሉት  ባለፉት ወራት ከግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ጋር በተያያዘ የገጠሙትን ችግሮች ለማስተካከል የሚያስችሉ ቁልፍ እርምጃዎች ተወስደዋል።

ከእነዚህም መካከል አዳዲስ የኮንትራት ውሎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር መፈፀቸው አንዱ ነው። 

ከዚህ በፊት የተስተዋሉትን የኃብት ብክነትና የፕሮጀክት አመራር ጉድለት እንዳይደገሙ በማድረግ ፕሮጀክቱን በሚፈለገው ጥራትና በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ መትጋት የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

የሚመለከተው አካል እስከ መስክ የዘለቀና ሥራውን በቅርበት የሚመራ የፕሮጀክት አስተዳደር ማሰማራት አለበት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋጣለት ተግባር መፈፀም ይቻል ዘንድም ጠንካራ ቅንጅት መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

አቶ ደመቀ እንዳሉት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ተርባይኖችን በመጠቀም የቅድመ-ኃይል ማመንጨት ስራ ይጀመራል ተብሎ የተያዘ እቅድ በተያዘው ጊዜ እውን መሆን አለበት።

ከአሁን በኋላ ግድቡን ለማጠናቀቅና ወደስራ ለመግባት ሌላ ተጨማሪ የፕሮጀክት ማራዘም ሊሰማ አይገባም ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው በተለይ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ቀደም ሲል የነበረው ጉድለት እንዳይደገምና ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት እንዲኖረው የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል ነው ያሉት።

ከእነዚህም መካከል በተለይም በብረታብረትና ተያያዥ የኢንጂነሪንግ ሥራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቁሳቁስ በመጠቀም ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ግንባታ ማከናወን ይችላሉ የሚባሉ ኩባንያዎች መምረጥ ነው።

ምልመላው የተካሄደው በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መመዘኛ መሰረት መሆኑንም ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት ከግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ጋር በተያያዘ የሚስተካከሉና የሚሻሻሉ ተግባራት አሉ። 

ፕሮጀክቱን በተያዘው ጊዜና በሚፈለገው ጥራት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግ ጠቅሰው በዓለም ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ መሰል ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለውጤት የሚበቁት ከሰባት እስከ 10 ዓመት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፈው ነው ብለዋል።   

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ግድቡ አሁን ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ለተሳታፊዎቹ ባቀረቡት ሪፖርት የአጠቃላይ ሥራው 65 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ከአጠቃላይ የግድቡ ሲቪል ሥራ 82 በመቶው ያህል የተጠናቀቀ ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ግን 23 በመቶ መሆኑን አንስተዋል። 

ስራው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በእስካሁኑ ሂደት ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም