ቀጥታ፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የባከነ የትምህርት ጊዜን ለማካካስ እየተሰራ ነው

ወለጋ  የካቲት  4/2011  በጸጥታ ችግር ምክንያት የባከነ የትምህርት ጊዜን በማካካስ የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት በስኬት ለማጠናቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ገለፁ።

በተቋሙ አሁን ያለው የተረጋጋ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተማሪዎቹና መምህራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ  ምልልስ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሲቪል ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ ፈይሳ ዋቅጂራ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ተረብሸው የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው በመስተጓጎሉ መጎዳታቸውን ተናግሯል።

አሁን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ተቋሙ ያመቻቸላቸውን የትምህርት ማራዘሚያ  ጊዜ በመጠቀም  የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ከመምህራን ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል ።

"ተረጋግቶ ለመኖርና ተምሮ ለውጤት ለመብቃት ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም መስራት ይጠበቅብናል " ብሏል ።

" ሴት ተማሪዎችን ከጸጥታ ጥቃት ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው በማደሪያችን አቅራቢያ ባዘጋጀልን የንባብና የጥናት ክፍል ያለስጋት መጠቀማችን በትምህርታችን እንድንበረታታ አድርጎናል" ያለችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የባንኪንግና ፋይናንስ ተማሪ አይናአዲስ ዘላለም ናት።

በተቋሙ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ናቶ በላቸው በበኩሉ በምዕራቡ ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የዜጎች መፈናቀልና የመንገድ መዘጋት ጋር ተያይዞ በመማር ማስተማር ሥራ ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበር አስታውሷል ።

"ተማሪዎች በመልካም ስነ-ምግባር ከግቢ ሳንወጣ በመቆየታችንና ተወያይተን መግባባት ላይ በመድረሳችን ትምህርታችንን ቀጥለናል" ብሏል።

ተማሪ ናቶ እንዳለው ዩኒቨርሲቲው የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው።

የተማሪዎች ህብረትም የተማሪዎችን ጥያቄ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኝና የመንፈቅ ዓመቱን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በስኬት ለማጠናቀቅ  እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

"ተማሪው ወደዩኒቨርሲቲው የመጣበትን የትምህርት ዓላማ ለማሳካት መትጋትና  መምህሩም  ኃላፊቱን በተገቢው መወጣት ይኖርበታል" ብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስራ ጥቆማ፣ የምክር አገልግሎትና የተግባር ትምህርት ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አፈታ በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ለተወሰነ ጊዜ ተስተጓጉሎ የነበረውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ በሳምንት እረፍት ቀናት ጭምር ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

"የመማር ማስተማር ሰራው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛክል " ያሉት ዳይሬክተሩ ተማሪዎች በጥሩ ስነምግባር ለውጤት እንዲበቁ መምህራን፣ የተማሪዎች ህብረትና የተቋሙ አስተዳደር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እየደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትምህርት ዘመኑ መግቢያ ተማሪዎችን በመቀበል ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተርና መምህር አቶ ያሬድ ደሳለኝ ናቸው።

በመሃል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር  የባከነውን የትምህርት ጊዜ በማካካስ የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት በስኬት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

"የተማረው የሰው ኃይል ከመንግስት ጎን በመሆን ትምህርትን የሚያደናቅፉ ተግባራትን በመከላከል ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብልናል” ብለዋል

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘላለም አብዲሳ  በበኩላቸው በምዕራቡ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ለተወሰነ ጊዜ የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ የሁለት ሳምንት ማራዘሚያ ተደርጓል ።

በእረፍት ቀናትም ጭምር የማካካሻ ትምህርቱ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ  ለሴት ተማሪዎች ልዩ የማጠናከሪ ትምህርት መዘጋጀቱን የገለፁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማስቀጠል ከተማሪዎችና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር  ስምምነት ላይ ተደርሶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም የበኩሉን አስተዋፆ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

በ1999 ዓ.ም 851 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛና ተከታታይ የትምህረት መርሀ ግብር በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ 38 ሺህ ተማሪዎች በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም