ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ከአምስት በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግባለች - ተ.መ.ድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ከአምስት በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግባለች - ተ.መ.ድ
አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ማስመዝገቧን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት አመለከተ።
ይሁን እንጂ በነፍስ ወከፍ ገቢ ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገራት ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የድርጅቱ ሪፖርት ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2018 የዓለም ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ በተመለከተ የተሰናዳው ሪፖርት ዛሬ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ይፋ ሆኗል።
ሪፖርቱ እንዳመላከተው፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት (2018) በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ከአምስት በመቶ በላይ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ማስመዝገብ ችላለች።
ለዚህም ደግሞ መንግሥት በመሰረተ-ልማትና በግንባታው መስክ የሚያፈሰው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይና የኢንቨስትመንት ሥራ መሆኑን ተመልክቷል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉት የተለያዩ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዎች ለእድገቱ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በአከባቢው ባለ ግዙፍ ምጣኔ ኃብታዊ ባለቤት እንደሚያደርጋትም ነው የተጠቆመው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የታየው የፖለቲካ መረጋጋት በአገሪቱ ኢንቨስትመንትና ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የገንዘብ መጠን እንዲጨምር ያስችላል ተብሏል።
ያም ሆኖ በዓለም ደረጃ የዶላር ዋጋ ማሻቀብ በተለይም የውጭ ንግድ ላይ ለተሰማራችው ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሊያስከትልባት እንደሚችል ተሰግቷል።
ይህም የኢትዮጵያ የብር ዋጋ ሊያሽቆለቁል እንደሚችልም በሪፖርቱ በስጋት ተቀምጧል።
በዓለም ገበያ ላይ የቡና ዋጋ መቀነስም በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት እድገት ላይ አሉታዊ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ተገምቷል።
በተመሳሳይ ጂቡቲም እንደ ኢትዮጵያ ከአምስት በመቶ በላይ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት በማስመዝገብ በከፍተኛ እድገት ኢትዮጵያን ተጋርታለች።
በሌላ በኩል ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የምስራቅ አፍሪካ የእድገት ምጣኔ 6 ነጥብ 2 በመቶ ነበር፤ በአካባቢው የነፍስ-ወከፍ ገቢ ደግሞ 3 ነጥብ 1 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያም በነፍስ ወከፍ ገቢ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ሪፖርት አሳይቷል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አፍሪካ አጠቃላይ እድገቷ 3 ነጥብ 2 በመቶ ነበር፤ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ደግሞ አፍሪካ 3 ነጥብ 4 በመቶ ዓመታዊ እድገት ይኖራታል ተብሏል።