ለአፄ ኃይለስላሴ የቆመው ሃውልት መልካም ስራ ትውልድን ተሻግሮ እንደሚያስመሰግን ማሳያ ነው

76

አዲስ አበባ የካቲት 3/2011 ለቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ መታሰቢያ የቆመው ሃውልት መልካም ስራ ትውልድን ተሻግሮ እንደሚያስመሰግን ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የንጉሱ የልጅ ልጆች የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፣ ለሃውልቱ መቆም ጉልህ አስትዋጽኦ ያበረከቱትን አመስግነዋል።

አጼ ኃይለስላሴ ለአፍሪካ አንድነት መቋቋምና በአህጉሪቱ አገራት መካከል አንድነት እንዲጎለብት ላበረከቱት አስተዋጽዖ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ሃውልት ቆሞላቸዋል።

ሃውልቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ፣ አፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶችና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ፣ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህመትና በጋናው ፕሬዝዳንት ናና አዶ አኩፎ ተመርቋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳሚዎችና የልጅ ልጆቻቸው እንዳሉት ከአጼ ኃይለስላሴ አበርክቶት አንጻር የሚገባቸውን ክብር ነው ያገኙት።

በአፍሪካ አገራት መካከል የወንድማማችነት ስሜት እንዲጎለብትና የአፍሪካ አንድነት እንዲቋቋም ያደረጉት ጥረትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

አርቲስትዘለቀ ገሰሰ እንደገለፀው “እርሳቸው በተለይ ለአፍሪካ የሰሩት፣ ለጥቁር ህዝብ ዓለም ላይ ላለው ሁሉ፤ ያወቅነው ምዕራባያዊያን ጋር ስንሄድ ነው። በእውነት ይሄ ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም ቢሆን ኩራት ነው፤ ለምን ጥሩ ጥሩ የሰራነው ታሪክ መደገፍ አለበትና በዚያው ደረጃ ዛሬ ይሄ መደረጉ ትልቅ ጅማሮ ነው። ከወደኋላ የነበረውን ትልቁን ታሪካችን እያወደስን ስንሄድ ለአዲሱም ትውልድ ጥሩ ይሆናል ብዬ አምናለሁ በጣም ደስ የሚል ቀን ነው።’’ብሏል

"በእርግጥ ይህ ሃውልት ዛሬ መቆሙ በጣም ታሪካዊ ነው፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ቀደም ብሎ መቆም የነበረበት ሃውልት ነበር። ለአፍሪካ ህብረት እዚህ እንዲቋቋም ላደረጉት ትልቅ አስትዋጽዖ ለኢምፐረር ኃይለስላሴ ይሄ የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም"ያሉት የአፍሪካ ህብረት ሰራተኛ ሚኒልክ ኢየሱስ ነው፡፡

በስፍራው አግኝተን ያነጋገርናቸው የልጅ ልጆቻቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለሃውልቱ መቆም የተለየ ድርሻ የነበራቸውን አመስግነዋል።

አፄ ኃይለስላሴ የልጅ ልጅ ልዑል መስፍን በሰጡት አስተያየት "እኔ የልጅ ልጅ ብቻም ሆኜ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያገለገሉ ከጣልያን ጦርነት ጀምሮ ነጻ ያወጡ ንጉስ ናቸው ። በዛ ላይ ደግሞ አፍሪካን ከነጭ አገዛዝ ስር ያወጡ ንጉስ ናቸው። በተለይ ከኑክሩማ ጋር ሆነው የሰሩት ስራ በኛ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም በዓለምም የሚታወስ ነው።’’ብለዋል፡፡

"ይሄ የብዙ አፍሪካዊያንና ኢትዮጵያዊያንም ደስታ ጭምር ነው፤ በተለይ የጋና ፕሬዝዳንት ትልቅ ክብር ይገባቸዋል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ አህመድ ይህን በማስፈጸማቸው ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማን።’’ ያሉት ደግሞ የአፄ ኃይለስላሴ ሌላው የልጅ ልጅ ኤርምያስ ሳህለስላሴ ናቸው፡፡

የአፄ ኃይለስላሴ የልጅ ልጅ ልዑል መስፍን በበኩላቸው "ማመስገን የምፈልገው የአፍሪካ ህብረትን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በትልቅ ትጋት ተሰርቶ እንዲቋቋም ላደረጉት፣ መፍቀዳቸው ብቻ ትልቅ ነውና እርሳቸውን ከልቤ አመሰግናለሁ ።’’ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም