በመቀሌ ከተማ ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሥራ ተጀመረ

46

መቀሌ የካቲት 3/2011 በመቀሌ ከተማ ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሥራ መጀመሩን የከተማው ኮንስትራክሽን፣ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም ሐዱሽ  ለኢ ዜ አ እንዳስረዱት በከተማው ሥራው የተጀመረው 11 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚሸፍን መንገድ ላይ ነው።

በከተማዋ ሰባት ክፍለ ከተሞች ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች ተመልምለውና ስልጠና ተሰጥቷቸው በሥራው መሰማራታቸውን ተናግረዋል። 

ወጣቶቹ በ35 የልማት ቡድኖች ተደራጅተው ወደ ሥራው መግባታቸውንና ለእያንዳንዳቸው በጨረታ ከ650 ስኩየር ሜትር እስከ 730 ስኩየር ሜትር ተከልሎ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ሥራው በዘፈቀደ በመስራቱ ይፈጠር የነበረውን የጥራት መጓደልና የጊዜ መጓተት ችግር እንዳይፈጠር ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አቶ ተስፋዓለም ገልጸዋል።

የግንባታ ስራውን ጥራትና ፍጥነት የሚቆጣጠር ካውንስል መቋቋሙንም ኃላፊው ተናግረዋል።

''የህዳሴ'' የልማት ቡድን አስተባባሪ ወጣት መሰረት ታደሰ እንደገለጸው በሥራው የሚያገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ለመሸጋገር አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግሯል።

የመሰቦ ልማት ቡድን አስተባባሪ የሆነው ወጣት ገብረ እግዚአብሔር ተካ  በበኩሉ "የድንጋይ ማንጠፍ ሥራው በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተሰጠንን ስልጠና ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችለን ነው" ብሏል።

በመቀሌ ከተማ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የድንጋይ ማንጠፍ ሥራ 167 ኪሎ ሜትር መንገድ ለአገልግሎት መብቃቱን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም