ቀጥታ፡

በሱዳን አቢዬ ግዛት ህይወታቸው ያለፈው ሶስት ኢትዮጵያዊያን የሰላም አስካበሪ አባላት አስከሬን ወደአገር ቤት ተላከ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2011 በሱዳን አቢዬ ግዛት የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ልኡክ አባል የሆኑትና ህይወታቸው በአደጋ ያለፈው ሶስት ኢትዮጵያዊያን አስክሬን ወደአገር ቤት ተላከ።  

ትናንት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባላትን ጭኖ የተለመደ እለታዊ ተግባሩን በማከናወን ላይ እያለ ነው
ሄሊኮፕተር በድንገት ተከስክሶ አደጋው የደረሰው።

በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ 10 የልኡኩ አባላት ላይም ጉዳት የደረሰ ሲሆን ክፉኛ ጉዳት የገጠማቸው ሶስት አባላት ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል።

7ቱ ግን እዛው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

አስክሬኑ ከስፍራው ሲነሳ በተመድ ሰላም አስከባሪ ልኡክ አባላት የክብር ወታደራዊ ሽኝት እንደተደረገለት ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የተመድ የአቢዬ ሰላም አስከባሪ ኃላፊ ሜጄር ጄኔራል ገብሬ አድሃነ የአደጋው መንስሄ እየተጣራ መሆኑን ጠቅሰው ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኖዬ ጉታሬዝ ዛሬ በተጀመረው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ለሞቱት የሰላም አስከባሪ አባላት የተሰማቸውን አዘን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ አወዛጋቢ በሆነችው የሱዳኗ አቢዬ ግዛት ወደ4 ሺህ 500 ያህል የሰላም አስከባሪ አባላትን በመንግስታቱ ድርጅት አማካኝነት  አሰማርታለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም