ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን በወላይታ ድቻ ሁለት ለባዶ ተሸነፈ

ሶዶ  የካቲት 3/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የ15ኛው ሳምንት ውድድር ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ለባዶ በሆነ ውጤት አሸነፈ።

ወላይታ ድቻ ሊጉን በ26 ነጥብ መምራት ላይ የነበረውን ክለብ ያሸነፈው ከዕረፍት በፊትና በኋላ ባስቆጠራቸው ግቦች ነው።

ለድቻ ግቦቹን በ20ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ፣በ75ኛ ደቂቃው ሁለተኛዋንና የመጨረሻውን ግብ  ደግሞ ፀጋዬ አበራ አስቆጥሯል፡፡

በውጤት ቀውስ ምክንያት ዋና አሰልጣኙን ዘነበ ፍስሃን በማሰናበት በጊዜያዊ  አሰልጣኝ ወደሜዳ የገባው ድቻ ፈጣን የኳስ ንክኪና የማጥቃት  እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

ተደጋጋሚ ግብ ሙከራዎችንን በማድረግም ተጋጣሚውን ሲያስጨንቅ ውሏል፡፡

ጊዮርጊስ  በበኩሉ መከላከልን መሠረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከረ ሲሆን፣ አጥጋቢ የግብ ሙከራ አላደረገም፡፡

የድቻ  ጊዜያዊ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ክለቡ የመሥመር አጨዋወቱን በማጠናከርና የግብ ዕድሎችን ባለማባከን  ውጤታማ ሆኖ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ስትዋርት ሆል ቡድናቸው ባሳየው እንቅስቃሴ ደስተኛ አለመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በቂ የግብ ዕድሎችን ያለመፍጠርና የተገኘውንም አጋጣሚ አለመጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ገልጸው፣ በዳኝነቱ ላይም ቅሬታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ዮናስ ካሣሁን በመሃል ዳኝነት የመሩትን ጨዋታ ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ በመከታተል ቡድኖቻቸውን አበረታተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በሶዶ ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ተከታትለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም