ወጣቱን ከአልባሌ ቦታዎች ለመከላከል የንባብ ባህልን ማሳደግ ያስፈልጋል-ኤጀንሲው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱን ከአልባሌ ቦታዎች ለመከላከል የንባብ ባህልን ማሳደግ ያስፈልጋል-ኤጀንሲው
ጎንደር የካቲት 3/2011 ወጣቱን ከአልባሌ ቦታዎች ለመከላከል የንባብ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ አስታወቀ።
አገር አቀፍ የንባብ ሳምንት ትናንት በጎንደር ከተማ "ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!" በሚል መሪ ቃል ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ወጣቱን ከአደንዛዥ እፆችና አልኮል ሱሰኝነት ለማውጣት የንባብ ባህሉን እንዲያሳድግ መርዳት ያስፈልጋል።
የንባብ ባህል እያደገ ሲሄድ ከሱሶች እንደሚወጣና በአልባሌ ቦታዎች መዋል እንደሚቀንስም ተናግረዋል።
ወጣቱ ለንባብ ያለውን ፍላጎት ለመጨመርም መጻህፍትን ከማቅረብ ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው ብለዋል።
በሳምንቱ በከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፣ጉብኝትም ይደረጋል።
ታዋቂ ደራሲያን የሕይወት ተሞክሯቸውን እንደሚያካፍሉም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው ሳምንቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ዝቅተኛ የማንበብ ባህል እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከ4 ሺህ በላይ መጻህፍት ለትምህርት ቤቶች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ለህዝብ ቤተ መጻህፍት ይለግሳል ብለዋል፡፡
ኤግዚቢሽንና የመጻህፍት ሽያጭ እንደሚካሄድ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ባለሀብቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ድርጅቶች መጻህፍትን በመግዛት እንደሚለግሱ አመልክተዋል።
በመጻህፍት ኅትመት፣ በመዛግብት አያያዝና ፋይዳ፣ በንባብ ባህል ዙሪያ፣ በቤተ መጻህፍት ሚና እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡
እስከ የካቲት 7/2011 በሚቆየው ሳምንት በጎንደር ዩነቨርሲቲና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ የተዘጋጀ ነው።
በዝግጅቱ አታሚዎች፣ አሳታሚዎች፣ የመጻህፍት አከፋፋይና መደብሮች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ ደራሲያን፣ የትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙኃን ይሳተፋሉ፡፡
ሳምንቱ የማህበረሰቡን የማንበብ ባህል ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር በየዓመቱ ይዘጋጃል።
በኢትዮጵያ የንባብ ሳምንት የተጀመረው በ2006 ነበር።