ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሥራ ፈላጊ ህዝብ ቁጥር አንድ ቢሊዮን ሊደርስ ይችላል - የአፍሪካ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ  የካቲት 3/2011 በአፍሪካ 705 ሚሊዮን የሆነው ዕድሜው ለሥራ የደረሰ ህዝብ ቁጥር በመጪዎቹ 12 ዓመታት ወደ አንድ ቢሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታወቀ።

ይህም የአህጉሪቱን የሥራ አጥነት ችግር ሊያባብሰው እንደሚችል ባንኩ ትናንት በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገውና የአህጉሪቱን ዓመታዊ የምጣኔ ኃብት ሁኔታ የሚዳስሰው ሪፖርት አመልክቷል። 

በአፍሪካ አገራት የሰው ኃይል ገበያ ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አዲስ ሥራ ፈላጊዎች መግባታቸው በአህጉሪቱ ሥራ የመፍጠር ተግባር ላይ ያለውን ጫና እንደሚያባብሰው ሪፖርቱ አትቷል። 

የሥራ ፈላጊው ቁጥር ዕድገት አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ አፍሪካዊያን በየዓመቱ 12 ሚሊዮን አዲስ ሥራ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ሪፖርቱ አሁን ባለው ሂደት ሥራ መፍጠር የሚቻለው ለግማሾቹ ብቻ ነው፤ እነርሱም ቢሆኑ ሊሰማሩ የሚችሉት መደበኛ ባልሆነ የሥራ መስክ ነው።

ይህ የሚያሳየው ከ100 ሚሊዮን የሚልቁ ወጣቶች ሥራ አጥ እንደሚሆኑ ነው ይላል ሪፖርቱ።    

በሪፖርቱ መሰረት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአፍሪካ የተመዘገበው ፈጣን ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተመሰረተ አይደለም።

የሥራ አጥነት ችግርን ለመቀነስ ጠንካራና ዘላቂነት ያለው የምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትን የማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት  አሳስቧል።

ከዚህም ሌላ የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ኃብታቸውን ኢንዱስትሪ የሚመራበትን ፖሊሲ መፍጠር እንዳለባቸው መክሯል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት መሰረት የአህጉሪቱ አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት በተያዘው የፈረንጆች አመት ወደ አራት በመቶ ያድጋል።

በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት የአህጉሪቱ አጠቃላይ የምርት ዕድገት 3 ነጥብ 5 በመቶ ነበር።

በተያዘው ዓመት ግን ይህ አሃዝ ወደ አራት በመቶ የሚያድግ ሲሆን በተከታዩ 2020 ደግሞ 4 ነጥብ 1 በመቶ ይደርሳል ተብሏል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዕድገትም ከነበረበት 5 ነጥብ 7 ወደ 5 ነጥብ 9 ከፍ እንደሚል ሪፖርቱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም