የሀገሪቱ የመንግሥታት አገዛዝ ሴቶች “ፖለቲካን በሩቁ” እንዲሉ አስገድዷል- ፖለቲከኞች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሪቱ የመንግሥታት አገዛዝ ሴቶች “ፖለቲካን በሩቁ” እንዲሉ አስገድዷል- ፖለቲከኞች
የካቲት 3/2011 በኢትዮጵያ በተለያዩ ግዜያት የነበሩት መንግስታት ሴቶች ከፖለቲካ እንዲሸሹ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተናግረዋል።
በአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የሴቶች ተሳትፎ አስተባባሪ ወይዘሪት ከውሰር እንድሪስ እንደገለጸችው ከዚህ ቀደም በፖለቲካው ያሉ ሴቶች የወንዶችን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ እንጂ የሴቶች የእኩልነት መብቶቻቸውን ይዘው የመሳተፍ እድል አልተፈጠረላቸውም።
“አሁን ባለንበት ሁኔታ ፖለቲካ ሲታሰብ ስቃይ እና መታሰር ነው ወደ አዕምሮ የሚመጣው፤ሴቶች ራሳቸውም ልጆቻቸውም በፖለቲካ ምክንያት ለእስር መዳረጋቸው ከፖለቲካ እንዲሸሹ አድርጓል” ነው ያለችው።
በማህበረሰቡ ውስጥ በፖለቲካ መሳተፍ እንደማያሳስር በተግባርም በግንዛቤም ደረጃ መያዝ ሲቻል ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጻለች።
መንግሥት በካቢኔ ደረጃ ግማሽ ያህሉን ሴቶችን መሾሙ ብቻ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን መሻሻል ያሳያል ብሎ መደምደም አስቸጋሪ እንደ ሆነ የተናገረችው ወይዘሪት ከውሰር እስከወረዳ ድረስ ሴቶች በሀገራቸው ጉዳይ ሀሳብ አመንጪና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ መሰራት አለበት ብላለች።
የመድረክ ለአንድነት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው አፄ ሃይለ ስላሴ ከሥልጣን በወረዱበት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው አቢዮት ላይ ሴቶች ጉልህ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ከአቢዮቱ በኋላም በርካታ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ሲሳተፉ እንደነበር ነው ያነሱት።
ሆኖም በደርግ ዘመነ መንግሥት ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር በሚል በርካታ ሴቶች ግፍ እንደተፈጸመባቸው፤ ኢህአዴግም በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉትን ሴቶች እያሰረ ማሰቃየቱ ሴቶችን ከፖለቲካ እንዲርቁ ማድረጉን ፕሮፌሰር መረራ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያንኳስስ መንግሥታዊና ማህበረሰባዊ ልማድ ገቢራዊ ሲሆን ቆይቷል።
አቶ ፈቃዱ እንደሚሉት ለሴቶች የትምህርት እድል አለመስጠት፣ ሴቶች በፖለቲካ እንዳይሳተፉ የሚያስገድዱ በማህበረሰቡ የሚነገሩ ተረትና ምሳሌዎች መኖራቸውንም በማሳያነት ያነሳሉ።
ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ቦታ አልነበራትም ያሉት ምክትል ሃላፊው ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሴቶች ተሳትፎ እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ብቃት ያላቸው፣ በትምህርት የላቁ፣ የአመራርነት ሚናቸው ከፍ ያሉ ሴቶች የአስፈጻሚውን፣ የህግ ተርጓሚውንና የህግ አውጪ አካላትን መቀላቀላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የሴቶች ተሳትፎ ወንዶች ለፖለቲካ ሹመት የሚጠቀሙበት እንጂ በራሳቸው ነጻ ፍላጎትና ተነሳሽነት ለእኩልነት መብቶቻው ተሳትፎ እያደረጉ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር መረራ አሁን ሴቶችን ወደ ስልጣን ለማምጣት የሚደረገው ሙከራ ዘለቂነቱ አስተማማኝ አይደለም ይላሉ።
አቶ ፍቃዱ በበኩላቸው በኢህአዴግ ካሉት አደረጃጀቶች የሴቶች ሊግ ጠንካራና ለውጥ እያመጣ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው በአራቱ አባል ድርጅቶች ጠንካራ ሴት አመራሮች መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።
የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የሚወሰነው በመንግሥት የስራ ሃላፊነቶች በመመደብ ውሳኔ ሰጪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ በማድረግ እንደሆነም አቶ ፍቃዱ ይገልጻሉ።
በፌደራል ደረጃ ሴቶች 50 በመቶ አስፈጻሚውን አካል እንዲይዙ የተደረገው ሥራ እስከ ወረዳ ድረስ እንደሚተገበርም ጠቁመዋል።
ከህዝብ ቁጥር ግማሹን የሚይዙትን ሴቶች ሳያካትት የሚጓዝ መንግሥት አይሳካለትም ያሉት አቶ ፈቃዱ፤ አሁን ፈር ቀዳጅ በሆነ መልኩ ወደ ውሳኔ ሰጪነት መጥተዋል ብለዋል።
መንግስት ለኮታ መሙላት ብቻ ሳይሆን ጥራትና ብቃታቸውን፣ የትምህርት ደረጃቸውን፣ የተሻለ የአመራር ብቃት ያላቸውን ሴቶች ወደ አስፈጻሚው አካል እያመጣ መሆኑንም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው “እንደ መድረክ ላለፉት 40 ዓመታት የቆየው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚለቅ ባይሆንም የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማሳደግ ሙከራዎችን እያደረግን ነው” ብለዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳካት ከአምስት አባላት ቢያንስ ሁለቱ ሴቶች እንዲሆኑ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ወይዘሪት ከውሰር ገልጻለች።
“ሴቶች በወንዶች የተሞላውን ፖለቲካ መቀላቀል አለባቸው፤ የፖለቲካ አየሩን ለብዙ ዓመታት የያዙትን ሰዎች ለመቀየር ሴቶች ወደፊት መምጠጣት አለባቸው ነው“ያለችው።
ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት ስለሚችሉ ወደ መድረኩ ለማምጣት ጥረት መደረግ አለበት ያለችው ወይዘሪት ከውሰር የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከጾታ እኩልነት ጀምሮ ግንዛቤ የመፍጠርና የአደባባይ ሰዎች እንዲሆኑ መሰራት አለበት ብላለች።
እነዚህን ለማሳካትም ሴት ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሊያበረክቱ እንደሚገባም አስተያየቷን ሰጥታለች።