ቀጥታ፡

በአዳማ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በአዲስ መልክ መደራጀቱ ተጠቆመ

አዳማ የካቲት 2/2011 በአዳማ ከተማ ያለውን የተረጋጋ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መደረጉን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው ከከተማዋ 18 ቀበሌዎች ከተወጣጡ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አባላት ጋር የከተማዋን አስተማማኝ ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ተወያይቷል።

በመምሪያው የማህብረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ኦፊስር ኮማንደር ሸዋዬ ደቻሳ እንደገለጹት በከተማዋ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን  የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አባላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

በከተማዋ አሁን ያለውን የተረጋጋ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በአዲስ መልክ ማደረጃት ማስፈለጉንም ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በነበረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትና ቅንጅታዊ አሰራር በከተማዋ መቀዛቀዙን ያስታወሱት ኮማንዳር ሸዋዬ፣ በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን በስፋት ያካተተ አዲስ መዋቅር በቀበሌ፣ በቀጠናና በጎጥ ደረጃ ተደራጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል።

የአዳማ ከተማ ህብረተሰብ የና የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስ ወንጀልና ህገ ወጥነትን በመከላከል በኩል ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀቱ አጋርነቱን ማሳየቱንም ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ አዲሱ የማህበረሰብ ፖሊስ አደረጃጀትና  በወቅቱ ተለዋዋጭ የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች ላይ በቂ ግንዛቤ  እንዲያገኝ ለማስቻልና ህዝቡን በማስተባበር በፀጥታው ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ጭምር ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን ሆኖ ህገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያ  ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ፣ ሌሎች ተያያዥ የሰላም ጠንቅ የሆኑትን እንቅስቃሴዎች አሁንም ነቅቶ በመጠበቅ ለከተማዋና አካባቢው ሰላም መስፈን ዘብ መቆም እንዳለበትም አስገዝበዋል።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደተስተዋለው ሁከት፣ ግጭትና ግርግር በከተማዋ እንዳይከሰት ከሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ ተችሏል" ያሉት ደግሞ የአዳማ ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለገሰ ዲሪሳ ናቸው።

"አሁን በከተማዋ አልፎ አልፎ የሚታየውን የስርቆት፣ ምንተፋ፣ ማጭበርበርና መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል መዋቅሩ በአዲስ መልክ መደረጀቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ለአዜአ አስተያየት የሰጡት የሉጎ ቀበሌ የማህበረሰብ ፖሊስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሀቢባ አማን በበኩላቸው እንዳሉት መደበኛ ፖሊስ ብቻውን የከተማዋን ሰላምና የህብረተሰቡን ደህንነት ማስጠበቅ አይችልም።

ህብረተሰቡ በአካባቢው ጉዳይ ላይ ችግሩን ከፖሊስ ይልቅ ለማህበረሰብ አቀፍ የፀጥታ አካላት ቀርቦ ማወያየቱና ጥቆማ መስጠቱ አዳማ ከተማ የተረጋጋች እንድትሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማው የተገኘውን አስተማማኝ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል አዲስ ኃይል መደራጃቱን የገለጹት ወይዘሮ ሀቢባ "መድረኩ በቀጣይ ስለምናከናውናቸው ተግባራት ግንዛቤ እንድንጨብጥ አድርጎናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም