በዩኔስኮ የተመዘገበው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ አደጋ ላይነው

164

አርባ ምነጭ  የካቲት 2/2011 የኦሞ እና የማጎ ብሔራዊ ፓርኮች በሰው ሰራሽ አሉታዊ ጫና ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ጥናቶች አመለከቱ።

ላለፉት ሦስት ቀናት በጂንካ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል፡፡

በመድረኩ ላይ በሁለቱም አንጡራ ሀብቶች ላይ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በብዝሃ ህይወትና በስነ-ምህዳር ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

ጥናቶቹ እንዳመለከቱት አንጋፋው የዱር እንስሳት መናኸሪያ በነበረውና በዩኔስኮ በተመዘገበው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ጥቅ ጥቅ ያለ ደንና ሣሮችን ሽፋን በማድረግ ከ70 በላይ አጥቢ እንስሳት ፣ ከ327 በላይ አዕዋፋት፣ ከ24 በላይ ተሳቢ እንስሳትና 3 የዓሣ ዝርያዎች ይገኙ ነበር፡፡

በተመሳሳይም በማጎ ብሔራዊ ፓርክ ከ237 በላይ አዕዋፋት፣ 14 የዓሣ ዝርያዎችና በርካታ የዝሆን ፣ የጎሽ ፣ የቀጭኔ ፣ የአንበሳ ፣ የአንብራይሌና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት መኖራቸው ተመልክቷል፡፡

ይሁንና ፓርኮቹ በሰው ሰራሽ አሉታዊ ጫና ምክንያት በአሁኑ ወቅት ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ጥናቶች አመለከቱ።

ኢንቨስትመንት፣ ህገ-ወጥ አደን፣ ልቅ ግጦሽ፣ ህገ-ወጥ ሰፈራና መሰል ችግሮች የፓርኮቹን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉት በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጥናቶቹ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በኢኮ ቱርዝም ልማት ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማጣቷንና በስነ-ምህዳርና በብዝሃ ህይወት ሀብት ላይ የከፋ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡

እንደ ሰጎን ፣ የሜዳ ፍየል ፣ ቀጭኔ ፣ ሳላ የመሳሰሉት ዝሪያቸው ከጠፉ ብርቅዬ እንስሳት መካከል እንደሚገኙበት ተብሏል፡፡

ከኦሞ ስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑሩ ይመር እንዳሉት የኦሞ ስኳር ፕሮጀክት 1፣ 3 እና 5ን የሚያገናኙ 183 ኪሎ ሜትር ካናሎች መሸጋገሪያ ድልድይ ባለመኖሩና በእርሻ ልማት ምክንያት እንስሳት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡

ከአገር ሽማግሌዎች መካከል የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደር ሎኩዋር ቲካፒል በሰጡት አስተያየት አርብቶ አደሩ የቤት እንስሳቱን ወደ ፓርኩ ይዞ ለመግባት እየተገደደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ወደ ኬኒያ ድንበር ሰፊ የገጦሽ ሣር ያለ ቢሆንም የታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወት ላይ አደጋ ከማድረሳቸው በላይ ከብቶቻችን እየዘረፉ በመሆኑ መንግስት ከሚመለከተው አካላት ጋር ሊወያይ ይገባል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን እንዳሉት በተደረሰው ስምምነት የፓርኮችን ህልውና ለመታደግ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ፣ ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሊንቀሳቀስ ይገባል።

ፓርኩም ሆነ የስኳር ፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጉ በመሆናቸው አንዳቸው በሌላቸው ላይ ችግር ሳያስከትሉ ልማት ለማከናወን ባለስልጣን መስሪያቤቱ፣ የፓርኩና የስኳር ፕሮጀክቱ ተጠሪዎች በጋራ እንደሚወያዩም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም