"የማንታረቀው ጠላት ቢኖር ድህነት ነው"----ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
"የማንታረቀው ጠላት ቢኖር ድህነት ነው"----ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት 2/2011 "የማንታረቀው ጠላት ቢኖር ድህነት ነው፤ በመሆኑም በቀንደኛው ጠላታችን ድህነት ላይ የከፈትነውን ግብግብ አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን " ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት ትናንት ከትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ፀለምት ወረዳ ከመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በማይ ፀብሪ ከተማ በተወያዩበት ወቅት ነው።
በውይይት መድረኩ ላይ የማይ ጸብሪና አካባቢው የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግርን ለመፍታት ከ147 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተጀመረው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መጓተትን ጨምሮ በርካታ የልማት ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ተነስተዋል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ዶክተር ደብረጽዮን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ እንዲፋጠንና በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለአገልግሎት እንዲበቃ ጉዳዩን ከሚመለከተው ቢሮ ጋር በቅረበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የገጠር መንገድን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄም በመንገድ ላልተሳሰሩት የገጠር ቀበሌዎች ቅድሚያ በመስጠት ግንባታውን ለማከናወን መወሰኑንና ሥራውም በቅርቡ እንደሚጀመር አመልክተዋል።
ተፈናቅለው በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ ወገኖች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶም ተፈናቃዮች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደሥራ እንዲገቡ በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለማሟላት የከልሉ መንግስት የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ማተኮሩንና የህዝብና የሀገር ቀንደኛ ጠላት በሆነው ድህነት ላይም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
"ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ርብርብ እንዲሳካም መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው" ያሉት ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ ይህን እውን ለማድረግ ህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር ደብረጽዮን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት መላው የክልሉ ህዝብ ልማቱና ሰላሙ የተረጋገጠ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከአካባቢው መስተዳድሮች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን በበኩላቸው እንዳሉት ወጣቱ ራሱን እንዲችል በመስኖ ልማት፣ በእንስሳት ሀብት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ በማኑፋክቹሪንግና በሌሎች የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ ተደርጓል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ውይይቱ ለስራና ልማት የሚያነሳሳና መግባባት የተደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል። ።
በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት ሊቀ ትጉሃን አገተ ተሻለ እንዳሉት በመድረኩ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋር የተደረገው ውይይት ፍሬያማና ተስፋ ሰጪ ነው።
ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ኑርአለም አደም በበኩላቸው "ሰላማችን ጠብቀን ልማታችን ለማስቀጠል ከመንግስታችን ጎን ተሰልፈን እንሰራለን" ብለዋል።
በመልካም አስተዳደር ላይ አተኩሮ የተካሄደው ውይይት ከመንግስት ጋር በመሆንና በመቀራረብ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት አጋዥ መሆናቸውንም ተናግረዋል።