ቀጥታ፡

በሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ውድድር የፌዴራል ና የአዲስ አበባ ፖሊስ ክለቦች አሸናፊ ሆኑ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 በሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች፤ አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል።

ከጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በሁለቱም ጾታዎች ከዘጠኝ ክለቦች የተወጣጡ 80 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል።

በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የተደረገባቸው ዘርፎች ናቸው።

ውድድሩ ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ፍፃሜውን ማግኘቱን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በውድድሩ ፌዴራል ፖሊስ በወንዶች፤አዲስ አበባ ፖሊስ ደግሞ በሴቶች አሸናፊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በነሐሴ 2011 ዓ.ም በሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በቦክስ ስፖርት ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመልመል ውድድሩ መካሄዱንም አቶ ስንታየሁ ገልጸዋል።

ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንና የመጀመሪያው ውድድር ህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ መካሄዱንም ባለሙያው አስታወሰዋል።

ከተማ መካሄዱንና ቀጣዮቹ ሁለት ውድድሮችም በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በጅግጅጋና በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ ብለዋል።

በአራቱ ውድድሮቹ የተገኘው አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ ይሆናሉ።

በሁሉም የክብደት ዘርፎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ እንዲሁም ለአጠቃላይ አሸናፊዎቹ የፌዴራል ፖሊስና አዲስ አበባ ፖሊስ ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።

የተዘጋጀውን ሽልማትም የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች ለተወዳዳሪዎቹ አበርክተዋል።

በህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው የዓመቱ የመጀመሪያ ብሔራዊ የክለቦች ውድድር የድሬዳዋ ከተማ የቦክስ ክለብ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።

ቀጣዮቹ ሁለት ውድድሮች በመጭው ሚያዚያ 2011 ዓ.ም በጅግጅጋና በሰኔ 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም