የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ የካቲት 2/2011 የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከህብረቱ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግረኒና ከወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሃብት ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዳሽን መስራች ቢል ጌትስ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ፌደሪካ ሞግረኒ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ቀደም ሲል በተወያዩበት ወቅት ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት፣ በፖለቲካውና በፖሊስ ማሻሻያዎች ለምታደርገው ጥረት ህብረቱ ሙሉ ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ለሌሎች አገሮች መልካም ተሞክሮ በመሆኑ የህብረቱ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ውይይቱን የተከታተሉት በኘሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ኘሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ስላለው የለውጥ ሁኔታ ገለጻ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቷ የህብረቱን ድጋፍ በማድነቅ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከማይክሮሶፍት መስራችና የዓለማችን ባለፀጋ ከሆኑት ቢል ጌትስ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ እያከናወነ ስላለው የስራ እንቅስቃሴ ባለሃብቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን በአትዮጵያ በተለይም በጤና፣በምግብና በግብርና ዘርፎች ከ250 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጉን ተናግረዋል።
ፋውንደሽኑ በአቅም ግንባታ፣ በጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት፣በግብርናው ዘርፍ በጥሩ አጋርነት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ባለሃብቱ ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ፕሬዝዳንቷም ፋውንዴሽኑ እያከናወነ ላለው በጎ ተግባር የመንግስት ድጋፍ እንደማይለይ ለባለሃብቱ ገልፀውላቸዋል።