ቀጥታ፡

ገብረክርስቶስ ቢራራ የደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ  የካቲት 1/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው የደቡብ ፖሊስ እግር ኳስ ኳስ ክለብ ገብረክርስቶስ ቢራራን የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

ክለቡ ከሳምንት በፊት የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩትን ዘላለም ሽፈራው(ሞሪኒዮ) በውጤት ማጣት ምክንያት ማሰናበቱ የሚታወስ ሲሆን አልአዛር መለሰ አዲስ አሰልጣኝ እስኪቀጠር የክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

የደቡብ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ ምክትል ኮማንደር ግርማ ዳባ ለኢዜአ እንደገለጹት ክለቡ ከገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር በመወያያት  እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ክለቡን እንዲያሰለጥኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል። 

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ ካለበት የወራጅ ቀጠና ወጥቶ በሊጉ ፉክክር  እንዲያደርግ አዲስ ተጫዋቾችን እንዲያስፈርምና ቡድኑ ያለበትን ክፍተት እንዲሞላ ከጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

አልአዛር መለሰም የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ደቡብ ፖሊስ እስካሁን 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 8 ነጥብ ብቻ በመያዝ 15 ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ የያዘው ደደቢት ከፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ስሑል ሽረ ጋር የተለያየውን ዳንኤል ጸሐዬ የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አስታውቋል።

ክለቡ ከሳምንት በፊት የቡድኑ አሰልጣኝ ከነበሩት ኤልያስ ኢብራሂም ጋር መለያየቱ ይታወሳል።

ዳንኤል ጸሐዬ በደደቢት እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ለመቆየት መስማማቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ገልጸዋል።

ክለቡ አሰልጣኙን የሾመበት ምክንያት ቡድኑ አሁን ካለበት የውጤት ቀውስ እንዲወጣና በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ ታስቦ እንደሆነ አመልክተዋል።

ዳንኤል የደደቢትን የታዳጊ ቡድን በአሰልጣኝነት፤ ዋናውን ቡድን በረዳት አሰልጣኝነትና በዋና አሰልጣኝነት እንደመራ አስታውሰው አሰልጣኙ የክለቡን ባህል የሚያውቁትና  በመሆኑና በወጣቶች የሚያምኑ በመሆኑ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ ተብለው ታምኖባቸዋል ብለዋል።

ደደቢት በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን 13 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ነጥብ ብቻ በመያዝ 16ኛ ደረጃን ይዞ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም