ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከ85 ቢሊዬን ብር በላይ ድጋፍ አገኘች

አዲስ አበባ  የካቲት 1/2011 ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 85 ነጥብ 6 ቢሊዬን ብር ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ።

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ26 ቢሊዬን ዶላር በላይ የውጭ ብድር እንዳለባት የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር የሀገሪቱን ውጭ ብድር መጠንና የሀብት አጠቃቀም በተለመከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ከወለድ ነጻና በዝቅተኛ ወለድ ብድር እያገኘች ሲሆን በእርዳታ መልክም የገንዘብ ድጋፍ አየተደረገላት ነው።

በተያዘው ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት ከበይነ መንግስታዊ ተቋማትና ከመንግስታት ትብብር 85 ቢሊዬን 629 ሚሊዬን ብር በብድርና በእርዳታ ድጋፍ አግኝታለች ብለዋል።

በዚህም መሰረት እንደ ዓለም ባንክ፣ አፍሪካ ልማት ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ አይነት በይነ መንግስታት ተቋማትና ከመንግስታት ትብብር  31 ነጥብ 833 ቢሊዬን ብር በብድር፤ 53 ነጥብ 796 ቢሊዬን ብር ደግሞ በእርዳታ በተጠቀሰው ወቅት መገኘቱን ገልጸዋል።

ከተለያዩ ተቋማትና የትብብር አጋሮች  የሚገኘው ብድር የወለድ መጠኑ  እስከ 75 ሳንቲም የሚደርስ በጣም ዝቅተኛና ከ40 ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ የሚከፈል መሆኑን አስረድተዋል።

ጣሊያን፣ እንደ አውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማት ለሚሰጡት ብድር የመክፈያ እፎይታ ጊዜ የሚሰጡ፣ ብድሩን ለመክፈል እስከ 40 ዓመት የሚፈቅዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ወለድ የምትበደረው ገንዘብ ለረጅም ዓመት የሚቆይ በመሆኑ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በራሳቸው ገንዘብ አመንጭተው እዳው እንዲከፈል እድል የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

"የውጭ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ መሆን አገሪቱን ወደከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ቢያስገባትም ያለባትን እዳ የመክፈል አቅሟን ግን አላሳጣትም" ብለዋል።

በዓለም ዓቀፍ የምጣኔ ኃብት መርህ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ አገሮች ምጣኔ ኃብታቸውን 56 በመቶ በብድር መሸፈን እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ሃጂ፤ የኢትዮጵያ ግን 44 በመቶ መሆኑን በማስረጃነት አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም