ቀጥታ፡

በኦሮሚያ የሚገኙ የግል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የጥራትና ብቃት ችግሮች ይታዩባቸዋል-ቢሮው

አዳማ  የካቲት 1/2011በኦሮሚያ የሚገኙ የግል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የጥራትና ብቃት ችግሮች እንደሚታዩባቸው የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በክልሉ በዘርፉ የተሰማሩ የ107 የግል ኮሌጆችን የውጤት ተኮር አሰራርን በአዳማ እየገመገመ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ተቋማቱ ችግሮቹ የሚታዩባቸው ውጤት ተኮር የሙያ ስልጠና አሰራርን ባለመተግበራቸው ነው።

ተቋማቱ አገሪቱ የደረሰችበትን የልማትና የእድገት ደረጃ የሚመጥን ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እንዳልቻሉም አስረድተዋል።

በዚህም የሙያ፣የዕውቀትና የክህሎት ችግሮች ያሉባቸውን መምህራንን በአነስተኛ ክፍያ  በብዛት በመቅጠርና ሥራቸውን እንደሚያከናወኑ ገልጸዋል።

በተቋማቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች የገበያ አዋጭነትና ተፈላጊነታቸው ዝቅተኛ እንደሆነም አቶ ኤባ ተናግረዋል።

ቢሮው መታረም ያልቻሉትን ተቋማት ከእውቅና መሰረዝና እስከ ፈቃድ መንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቀዋል።

የካኔኑስ ኮሌጅ ዲን አቶ አድማሱ ድሪባ የትምህርት ጥራት የዜጎች ጉዳይ በመሆኑ የግል ኮሌጆች ትምህርትን እንደ ንግድሥራ ማየት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።

"ተማሪ ወደ ግል ኮሌጅ ሲመጣ የትምህርት ማስረጃ እንደመግዛት አድርጎ የማየት ዝንባሌና አመለካከት አለው" ያሉት አቶ አድማሱ፣ ችግሩ ለትምህርት ጥራት ጉድለት መንስዔ ሆኗል ብለዋል።

የመማሪያ ቁሳቁስ ሳይሟላ ኮሌጅ ማቋቋም አግባብነት እንደሌለው የሚናገሩት ዲኑ፤ በአግባቡ የመማሪያ ቁሳቁስ ሳያደራጁ ኮሌጅ ለመክፈት የሚሞክሩ ባለሃብቶች እውቅና ሊሰጣቸው አይገባም ይላሉ።

የደንበል ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ባለቤት አቶ ተሾመ በቀለ በበኩላቸው ኮሌጃቸው የተሻለ እውቀትና ሥነ ምግባር ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ውጤታማ ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኮሌጁ 70 በመቶ የተግባርና 30 በመቶ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑ የጠቆሙት ባለሀብቱ፣ በኮንስትራክሽንና በሰርቬይንግ ሙያዎች ስልጠና የሚታየውን የላቦራቶሪዎችና ወርክሾፖች ችግር ለማቃለል  ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም