የጉምሩክ ፖሊስ ለማደራጀት 94 ኬላዎች ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
የጉምሩክ ፖሊስ ለማደራጀት 94 ኬላዎች ተለዩ
አዲስ አበባ የካቲት 1/2011 የወጪና ገቢ ኮንትሮባንድን ለመከላከል 94 ኬላዎች ተለይተው የጉምሩክ ፖሊስ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ባለሙያዎች መመደብ መጀመሩንና ፌዴራል ፖሊስም ከፍተኛ ችግር በሚስተዋልባቸው ቦታዎች ፖሊሶችን ለመመደብ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፉት ስድስት ወራት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ከ510 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድ ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ የሆነ የጉምሩክ ፖሊስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተላለፈ ውሳኔ ለማቋቋም እየተሰራ ነው።
የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ጅግጅጋ፣ ሞያሌና ሁመራ የወጪ ኮንትሮባንድ በከፍተኛ ሁኔታ ያለባቸው ቦታዎች መሆናቸው ተለይቷል።
ሞያሌ፣ ሀዋሳ ፣ ጅግጅጋ፣ ጋላፊና ሚሌ እንዲሁም ሁመራ ደግሞ የገቢ ኮንትሮባንድ ችግር የሚስተዋልባቸው ናቸው።
ሰሜን ምስራቁ ክፍልና ጋምቤላ ክልል ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት የሚስተዋልባቸው እንደሆነም አስረድተዋል።
በአገሪቱ በስፋት እየታየ ያለውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በመደበኛ የጉምሩክ ኬላ ተቆጣጣሪዎች ብቻ መግታት ስለማይቻል የጉምሩክ ፖሊስ ማደራጀት ማስፈለጉን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
የጉምሩክ ፖሊስ ለዚሁ ቁጥጥር ብቻ የሚመደብ ሲሆን አደረጃጀትና ስምሪቱ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ምክትል ዋና ኮሚሽነር የሚመራ ይሆናል።
ባቡርን ጨምሮ 94 መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ተለይተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ ችግሩ በስፋት ይስተዋልባቸዋል በተባሉ ቦታዎች የጉምሩክ ባለሙያዎች ማሰማራት መጀመሩን አብራርተዋል።
ለፌዴራል ፖሊስ በቀረበ ጥያቄ መሰረትም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ቦታዎች ፖሊሶችን ለማሰማራት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል ብለዋል።
ለየኬላዎቹ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል በማደራጀት በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።
በግማሽ ዓመቱ በተደረገው የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ የመከላከል ሥራ 442 ቀጥታ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።