በጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ የንብረት ውድመት አስከተለ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ የንብረት ውድመት አስከተለ
ጎንደር የካቲት1/2011 በጎንደር ከተማ ልዩ ስሙ አዘዞ አካባቢ ግራር ሰፈር ተብሎ በሚጠራው የእንስሳት ማድለቢያ ስፍራ በደረሰ የእሳት ቃጠሉ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የ5ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ኦፊሰር ምክትል ሳጅን መሀመድ ሰይድ ለኢዜአ እንደተናገሩት አደጋው ሊደርስ የቻለው ትናንት ከምሽቱ 5 ሰአት ላይ በማድለቢያ ስፍራው ከሚገኙ ክፍሎች በአንዱ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ነው፡፡
በቃጠሎው 20 የከብቶች ማድለቢያና የወተት ላሞች ማርቢያ የነበሩ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የተቃጠሉ ሲሆን 51 ከብቶችም በቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸው ሞተዋል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ህብረተሰብና ፖሊስ ከከተማው እሳት አደጋ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ምክትል ሳጅን መሃመድ ተናግረዋል፡፡
በእሳት ቃጠሎው የማድለቢያ ስፍራው ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን ለእንስሳት መኖነት የተዘጋጁ ፋጉሎና የሳር ድርቆሽ እሳቱን ለመቆጣጠር አዳጋች አድርገውት እንደነበር ምክትል ሳጅን ገልጸዋል፡፡
በአደጋው የሞተ ሰው እንደሌለ የገለጹት ምክትል ሳጅን መሀመድ የማድለቢያ ስፍራው በአካባቢው በማህበር የተደራጁ ከ20 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ሀብትና ንብረት መሆኑን ፖሊስ ማረጋገጡንም አስታውቀዋል።